ማውሪታኒያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ከኮሞሮስ ተረከበች።

37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ሲሆን የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማውሪታኒያ በ2024 የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት እንድትመራ የተመረጠች ሲሆን የሊቀመንበርነት ቦታውን ከ2023 የህብረቱ ሊቀመንበር ከነበረችው ኮሞሮስ ተረክባለች፡፡

የማውሪታኒያ ፕሬዝደንት መሀመድ ኦዉልድ ጋዞኒ ከወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ከኮሞሮሱ ፕሬዝደንት አዛሊ አሶውማኒ ተረክበዋል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ስልጣን የህብረቱ አባል ሀገራት በየዓመቱ እየተቀያየሩ የሚያገኙት ስልጣን ሲሆን ከህብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር በመሆን ስራን ማቀላጠፍ እንዲሁም አፍሪካን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የመሳተፍ ሀላፊነት አለበት፡፡

ፕሬዝደንት ኦውልድ ዛሬ የተመረጡት የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ረብዕ እና ሐሙስ ዕለት ባካሄዱት ጉባኤ እንዲመረጡ ይሁንታ ከሰጣቸው በኋላ ነው ተብሏል።

በጉባኤው በርካታ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች እና የአለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

የዘንድሮው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ትኩረቱን በትምህርት ልማት ላይ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በጉባኤው ላይ እንግድነት የተገኙት የብሪክስ መስራች የሆኑት የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቡድን 20 ሀገራት ውስጥ በአባልነት ሊካተቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ሉላ ያለአፍሪካ ተሳትፎ ዓለም ምንም ነች በማለት ነው የአፍሪካን ተሳትፎ ወሳኝነት የተናገሩት።

አፍሪካ ህብረትእንደ ተቋም ባሳለፍነው ዓመት በኢንዶኔዢያ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ አባል እንዲሆን ከስምምነት ተደረሰ ሲሆን ተጨማሪ ሀገራትም የዚህ ቡድን ሊሆኑ እንደሚገባ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ተናግረዋል፡፡

ህብረቱ ባወጣው መግለጫ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተጋበዙ ሀገራት እና ተቋማት ውጪ የሚመጡ ተሳታፊዎችን እንደማያስተናግድ አስጠንቅቋል፡፡

37ኛው የህብረቱ መሪዎች እና 44ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤን በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው ሀገራት እና ተቋማት ውጪ እንዳይመጡ እና ፈቃድ የተሰጣቸው ደግሞ ከአንድ ተወካይ በላይ እንዳይመጡ ሲልም ህብረቱ አሳስቧል፡፡

ከዚህ በፊት በአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች ላይ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ፈቃድ የተሰጣቸው ሀገራት እና ተቋማትም ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የጉባኤው አዘጋጅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ አማርኛ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ እንዲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቱር በኩል ከሰሞኑ ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *