የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር የስድስት ወራት ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ አለሙ ስሜ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ የሚደረገው ክልከላ ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ለፓርላማው እንደተናገሩት፥ ነዳጅ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎችን ለግል ጥቅማጥቅ ሆነ ለሌላ አላማ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚደረገውን እገዳ በጥብቅ እንደሚያስፈጽሙ ገልጸዋል።
ውሳኔው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ስጋቶች እና ከባህላዊ የነዳጅ ፍጆታ ጋር ተያይዞ እየጨመረ ለሚመጣው ወጭ ስልታዊ ምላሽ ነውም ተብሏል።
እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ወጪ ፖሊሲ አውጪዎች አገሪቱ በተለመዱት ተሽከርካሪዎች ላይ ያላትን ጥገኝነት እንዲገመግሙ እና የካርበን በካይ ጋዝ መጠንን ለመቀነስ ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚጣጣሙ መንገዶችን እንዲመረምሩ አድርጓል።
እገዳው የካርቦን ልቀትን ለመግታት፣ ንፁህ አየርን ለማስተዋወቅ እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን በአውቶሞቲቭ ሴክተር ላይ ማበረታታት በሚል መጣሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
እንደ አቶ አለሙ ገለጻ፣ ለአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት ያለው ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት እና ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የትራንስፖርት አማራጮች መሸጋገሩን ያሳያልም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደድር ከሁለት ወር በፊት ረጅም ዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ከአገልግሎት እንደሚያስወጣ መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባ ከፍተኛ ጭስ የሚለቅ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች አስቀድመው መፍትሄ እንዲያዘጋጁ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ድሪባ እንደተናገሩት የመኪና ጭስ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው የተባለ ሲሆን እያንዳንዱ መኪና የሚያስወጣው ጪስ ይለካል ተብሏል።
መኪናው ከተቀመጠው መለኪያ በላይ ጪስ የሚያመነጭ ከሆነ አገልግሎት እንዳይሰጥ ይደረጋልም ብለዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጭስ የሚለቁ ተሽከርካሪዎች ከተመረቱ 23 ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ስለዚህ አሮጌ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች ከአሁኑ መፍትሄ ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል።
በመዲናዋ አሮጌና ከፍተኛ ጭስ የሚለቁ በርካታ መኪኖች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ መኪናዎቹን በአንድ ጊዜ ሥራ እንዲያቆሙ ማድረግ እንደማይቻል አመላክተዋል፡፡
ሆኖም ቦሎ የሚሰጡ፣ መኪናዎችን የሚቆጣጠሩና መኪና የሚገዙ አካላት ባለሥልጣኑ የሚያወጣውን የጭስ ስታንዳርድ መሠረት እንዲያደርጉ አቶ ድዳ አሳስበዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ስታንዳርዱ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል። ስለዚህ አሮጌና ከፍተኛ ጭስ የሚለቅ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች ጭስ የሚቀንስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ወይም መኪናውን መቀየር ይኖርባቸዋል ተብሏል።
በዓለም የጤና ድርጅት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሀገራት የአየር ጥራት ስታንዳርድ ያዘጋጃሉ። አዲስ አበባም ይህን መሠረት ስታንዳርዶች እያዘጋጀች ነው ያሉት አቶ ድዳ፤ ይህም ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር ጥራት እንዲኖር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተሸከርካሪ እንዳለ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳይ ሲሆን አብዛኞቹ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው፡፡
ከአረጁ ተሸከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጋዝን ለመከላከል ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ አገልግሎት የሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ተጥሎባቸዋል፡፡
እንዲሁም አዲስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ መኪና አስመጪዎች ደግሞ ዝቅተኛ ግብር እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ ሲሆን በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ አዲስ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የበለጠ የግብር እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ያገኛሉ፡፡
በዓለም ላይ በአየር ብክለት ምክንያት ከሚደርስ የሰዎች ሞት ውስጥ 11 በመቶ ያህሉ ከተሽከርካሪዎች በሚወጣ በካይ ጋዝ ምክንያት እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡