በምግብ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ደብቆ ተጠርጣሪ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ግለሰቡ ከናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ የሄደው ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ነበር፡፡
ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ምግብ ይዞለት የሄደው ይኸው ተጠርጣሪ ከድፍረትም ድፍረት የሚያሰኝ ተግባር ነበር የፈፀመው፡፡
በወቅቱ በሳህን የተቋጠረው ምግብ እንጀራ ፍርፍር በማካሮኒ ነበር፡፡ በእነዚያ የማካሮኒ ቀዳዳዎች ውስጥ የሚያብለጨልጩ ነገሮች ተወታትፈዋል፡፡
ምግቡን ፈትሸው የሚያስገቡት የፖሊስ አባላት ባዩት ነገር ተጠራጥረዋል፤ ምግቡ ተዘርግፎ ሲፈተሽ ብዛት 51 የማካሮኒ ፍሬዎች በተጠቀለሉ የአልሙኒየም ወረቀቶች አባብጠዋል፡፡ ወረቀቶቹን በመፍታት ለማየት ሲሞከርም ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ግለሰቡ ከዚህ በፊት በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በዚያው ፖሊስ መምሪያ ታስሮ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ድፍረት በተቀላቀለበት ሁኔታ አደንዛዥ ዕፁን በምግብ ውስጥ ደብቆ ወደ ተጠርጣሪ ማቆያ ቤት ለማስገባት የሞከረው ጠያቂ ሰዎች የሚበዙበትን ሠዓት በማጥናት እንደነበር ተገልጿል፡፡
ዕጹን ሊያስገባ ሲል የተያዘው ተጠርጣሪም በፈፀመው ወንጀል የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ዘገባ ያሳያል።
በኢትዮጵያ የአደገኛ ዕጽ ወንጀሎች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን ፖሊስ በተለያዩ አካባቢዎች ዕጾቹን እየያዘ እና እያስገደ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ኤርፖርት ውስጥ በተደጋጋሚ አደገኛ ዕጾችን ደብቀው ከአፍሪካ ወደ እስያ እና ከደቡብ አሜሪካ ሀገራት ወደ ሌሎች ሀገራት ለማዘዋወር ሲሉ እየተያዙ ናቸው፡፡