የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለመስራት ካቀዳቸዉ 54 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ አስታወቀ
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን የ 2016 አመት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
አስተዳደሩ በወራቱ ለማከወን ካከቀዳቸዉ 54 ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴዉ ተናግረዋል።
በዚህም በስድስቱ ወራት የነበረዉ የዲዛይን ስራዎች አፈጻጸም 57 በመቶ ሲሆን ይህም ዝቅተኛ እንዲሆን እንዳደረገበት ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዉጭ አማካሪ ድርጅት ለተሰራ ስራ ክፍያ የዉጭ ምንዛሪ በመዘግየቱ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸዉንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በተለያዩ ምክኒያቶችም 84 ፕሮጀክቶች መቋረጣቸዉ እና ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ዉላቸዉ መሰረዙንም ተናግሯል።
የግብዓት እጥረት ፣ የወሰን ማስከበር ችግር እና የተጋነነ የካሳ ተመን ተቋሙ በወራቱ ካጋጠሙት ችግሮች ዉስጥ ችግር ሆነዉ መቀጠላቸውን አስረድተዋል። ሌላዉ አስተዳደሩ በመንገዶች ጥገና እና ግንባታ በወራቱ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በኢትዮጵያ 169 ሺህ 450 ኪ.ሜ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በየቦታው የጸጥታ ችግሮች እያጋጠሙ ሲሆን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ውስጥ 62 በመቶዎቹ በጦርነት የተፈናቀሉ ሲሆን መንገዶች በጸጥታ ችግሮች በመዘጋጋታቸው ምክንያት ከክልል ከተሞች ወደ አዲ አበባ ለተሸለ ህክምና መምጣት ባለመቻላቸው ህይወታቸው እያለፈ ላይ ይገኛል፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ዋነኛ የጸጥታ ችግሮች ያሉባቸው ክልሎች ሲሆኑ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ባሳለፍነው ሀምሌ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ኢንተርኔትም ሙሉ ለሙሉ እንደተቋረጠ ነው፡፡
አሁን ላይ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አስታውቋል፡፡