የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ አዲስ የዲፕሎማሲ ፍትጊያ መፍጠሩ ተገለጸ

በቀይ ባህር ላይ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ስትገልጽ የቆየችው ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ወደብ በሊዝ መግዛቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡

የሁለቱ አካላት የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ወደብ እና ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራት የሚፈቅድ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ይጠቅሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የ20 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይደረጋል የተባለ ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ ተጨማሪ ድርድሮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም ሶማሊያ የኢትዮጵያን እና የግዛቴ አካል ናት የምትላት ሶማሊላንድ ያደረጉት ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ዓለም አቀፍ ህግንም የሚጥስ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ያደረጉት ስምምነት ሶማሊያ አልሻባብን ለማጥፋት የጀመረችውን ዘመቻ እንደሚያስተጓጉል እና የሽብር ቡድኑ ዳግም እንዲያንሰራራ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ እንደምትወስድ የገለጸች ሲሆን ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ መሆኗን ህዝቡም ዝግጁ እንዲሆን ጥሪ አቅርባለች፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ እና ከዓረብ ሊግ መሪዎች ጋር በስልክ መወያየታቸውን የገለጹ ሲሆን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና አንድነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውም ተገልጿል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና አንድነትን እንደሚደግፍ ያስታወቀ ሲሆን የአፍሪካ ህብረትን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

ሶማሊላንድ ላለፉት 30 ዓመታት ራስ ገዝ አስተዳድር ሆና የቆየች ሲሆን የሀገርነት እውቅና እንዲሰጣት ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ህብረት ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡

አሜሪካ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮችን ለማድረግ የሚያስችላትን ፖሊሲ በኮንገረሷ ማጸደቋ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ለምዕራባዊያን ሀገራት ለማስረዳት የዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደምትልክ ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *