መንግሥት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ከእስር እንዲለቅ ሲፒጂ ጠየቀ

የኢትዮ ኒውስ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም የጸጥታ ክልሎች አራት ኪሎ በሚገኘው ከቢሮው አካባቢ እንዳሰሩት የስራ ባልደረባው እና ባለቤቱ ተናግረዋል።

የጋዜጠኞች መሽት ተሟጋች የሆነው ሲፒጂ ባወጣው ሪፖርት ጋዜጠኛ በላይ ከታሰረ ሶስት ሳምንት እንዳለፈው እና እስካሁን ፍርድ ቤትም እንዳልቀረበ አስታውቋል።

የሲፒጂ ሰብሰሀራ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ እንዳሉት በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የመስራት ነጻነታቸው መጎዳቱን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቅ ሲፒጂ አሳስቧል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት የጋዜጠኞችን እስር እንዲያቆምም ሲፒጂ ጥሪ አቅርቧል።

የጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ባለቤት በላይነሽ ንጋቱ ባለቤቷ አንድ ጊዜ ከታሰረበት ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሄዳ እንደጠየቀችው የተናገረች ሲሆን በአማራ ክልል ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አያይዘው እንዳሰሩት ነግሮኛል ማለቷ ተገልጿል።

ኢትዮ ኒውስ የተሰኘው ይህ የዩቲዩብ ሚዲያ በአማራ ክልል ያሉ ሁኔታዎችን በስፋት ከሚዘግቡ ሚዲያዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን የጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እስርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በየጊዜው ጋዜጠኞች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እየተያዙ ለእስር የሚዳረጉ ሲሆን ክስ ሳይመሰረትባቸው ለዓመታት በእስር ቤት ይቆያሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያ አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት ሀገር ተብላ ነበር።

ይሁንና ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ ሲሆን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

የፌደራል መንግሥት “የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም ማደራጀት” በሚል የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን ካፈረሰበት ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በክልሉ ጦርነት ተቀስቅሷል።

በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ይህ ጦርነት መስፋፋቱን ተከትሎ የክልሉ ሁኔታ ከአቅሜ በላይ ነው ማለቱን ተከትሎም ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተደንግጓል።

አሁን ላይ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ መሆኑን መንግሥት ቢገልጽም በበርካታ ቦታዎች ላይ ጦርነት እየተካሄደ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችም በመስተጓጎል ላይ ናቸው።

በአማራ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን መንግሥት የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት እየተጋፋ በመሆኑ ኢንተርኔት እንዲለቀቅ ተጠይቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *