600 ሚሊየን ዶላር ወጭ የሚደረግበት 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሊገነባ ነው፡፡
የንፋስ ሀይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ስምምነት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቱ አሜአ ፓወር ኩባንያ ጋር የስምምነት ፊርማ በዱባይ ተፈራርሟል፡፡
በሶማሌ ክልል አይሻ አካባቢ የሚገነባው የንፋስ ሀይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው እንደሆነ ተገልጿል።
አጠቃላይ የንፋስ ሀይል ማመንጫው 600 ሚሊየን ዶላር ወጭ የሚደረግበት ሲሆን አሜአ ፓወር በተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኩባንያ እንደሚገነባ ተጠቅሷል፡፡
ስምምነቱ በመንግስትና በግል አልሚዎች ማእቀፍ የሚሰራ ትልቁ ኢንቨስትመንት እንደሚሆን እንዲሁም በንፋስ ሀይል ማመንጫ ከምስራቅ አፍሪካ ግዝፉ ይሆናል ተብሏል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎቷን ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ ሀይል በማግኘት ላይ ስትሆን በትግራይ እና ኦሮሚያ ክልል ሶስት የንፋስ ሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከንፋስ ሀይል ብቻ 10 ጌጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያላት ሲሆን አሁን ላይ 324 ሜጋ ዋት ሀይል ከንፋስ ሀይል በማግኘት ላይ ትገኛለች።
ለሱዳን፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል እየሸጠች ያለችው ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም ለደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ታንዛኒያ ተጨማሪ ሀይል ለመሸጥ ድርድር እና የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የገንዘብ ሚንስቴር ገልጿል።