የጸጋ ተስፋዎች እና በህይወት የመኖር ትግል

ጸጋ ትባላለች በትግራይ ክልል ደንጎላት በተባለ አካባቢ የተወለደች ሲሆን እድገቷም ሆነ የትዳር ሕይወቷን በዚያው ያደረገች ወጣት እናት ናት።

ጸጋ ወደ ትዳር ስትገባ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበረች በወቅቱ በቤተሰብ ስምምነት በተፈጸመው በዚህ ትዳር 2 ሴት እና 2 ወንድ በአጣቃላይ 4 ልጆችን አፍርተውበታል። በወቅቱ በነበሩበት አካባቢ በቆሎ በማምረት እና በመሸጥ ከባለቤቷ ጋር ጥሩ ኑሮ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችም ነበሩ።

ነገር ግን ይህ ጥሩ የሚባለው ኑሮ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተገላቢጦች እየሆነ መጣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ነገሮች መስመራቸውን እየለቀቁ መጡ… በወቅቱ የንግድ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ መምጣታቸው መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች በተለይም ምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋቸው የማይቀመስ ሆነ እንደ ቡና፣ ጨው፣ ስኳር እና መሰል ነገሮችን ማግኘት ዘበትም ሆነ  ፡፡

በዚህ ሁኔታ ኑሮን መግፋት ያቃታቸው ወ/ሮ ጸጋ እና ባለቤቷ የነበራቸውን  ንብረት ቤተሰቦቻቸው ጋር አስቀምጠው ቤታቸውን ዘግተው 4 ልጆቻቸውን በመያዝ በሰላሙ ጊዜ የደርሶ መልስ ትኬት መግዣ በሚሆን ዋጋ ተሳፍረው አዲስ አበባን መዳረሻቸው አደረጉ፡፡ ይሁንና የጦርነቱ ዳፋ እዚህም ድረስ ተከትሎ የመጣ በመሆኑ እንዳሰቡት ኑሮ ቀላል አልሆነላቸውም።

የቤት ኪራይ፣ የ4 ልጆች ቀለብ ሌሎችም ይሔ ነው ተብለው በማይጠቀሱ ወጪዎች ከባድ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ገቡ።  መጀመሪያ ላይ ልጆቿን በመያዝ በልመና ትተዳደር የነበረችው ጸጋ ሥራ የለመደው አካሏ እና አይምሮዋ ይህን ለመቀበል ከብዶት እንደነበር ገልጻለች፡፡

ቀስ በቀስ ግን ከራሷ ጋ በመምከር ቀለል ያሉ የንጽህና መጠበቂያ እንደ ሶፍት አይነት ነገሮችን በመሸጥ ባለቤቷ ደግሞ መወልወያ እና መጥረጊያ በማዞር ኑሮን ለመግፋት እየሞከሩ ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ የሚሠሩት ሥራ ለቤት ኪራይ 4500 ወጪ አውጥተው ቀለብ እና ለልጆች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት የሚበቃቸው አልሆነም።  በአሁኑ ሰአት ልጆቿ ትምህርት መቀጠል እንዳለባቸው ብታምንም ነገሮች ግን ሊስተካከሉ ባለመቻላቸው ልጆቿ ከትምህርት ቤት ርቀዋል።

የጸጋ ታሪክ እንደ እድል ሆኖ መተዳደሪያቸው የነበረውን ልመና በማቆም ወደ አነስተኛ ሥራ ተሰማሩ እንጂ አሁን ላይ በከተማችን የሚስተዋለው ይኼ ነው።

በአሁኑ ሰአት በመዲናችን አዲስ አበባ በጦርነት እና ሌሎች ተፈትሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ከአማራ፣ ትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህም ሳቢያ በከተማዋ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎች ቁጥር በተለይም ሴቶች እና ሕጻናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል።

ጸጋን እንደምሳሌ አነሳን እንጂ በርካቶች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲለምኑ የሚታዩ ሲሆን መለመን ያልቻሉ ነገር ግን የተሻለ ድጋፍ ፍለጋ ወደ ከተማዋ የገቡ ዜጎችን የሚቀበል እና ድጋፍ የሚያደርግ አንድም ተቋም የለም፡፡

ከዚህ ቀደም ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተስፋፋ የመጣውን ልመና ያስቀራል የተባለ ” የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑ አይዘነጋም።

ይህ ሕግም ሲጠናቀቅ በአንድ ቋት ሰዎችን መርዳት የሚያስችል ስረአት እንደሚዘረጋና ከዚህ ውጪ የሚደረግ ምጽዋት ሰጪንም ሆነ ተቀባይን ተጠያቂ ያደረገ ህግ መዘጋጀቱ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ፣ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር እና ሌሎች የፌደራል ተቋማትን በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ብንሞክርም ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ነግረውናል፡፡

ይህንን ረቂቅ አዋጅ እና በአሁኑ ሰአት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው  በልመና የሚተዳደሩ ሴቶችና ሕጻናትን በሚመለከት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንዲሁም አደጋ እና ስጋት ሥራ አመራርን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በአዲስ አበባ 88,960 በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ ጎዳናዎች እንደሚኖሩ የከተማው አስተዳድር በ2015 ዓ/ም ያወጣው ጥናት ያስረዳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *