የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ሞላው

ህወሀት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝን ማጥቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው።

ለሁለት ዓመት የዘለቀው ይህ ጦርነት 800 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን እንዲያጡ ሲያደርግ 26 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራም አድርሷል።

ለዚህ ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው የሰላም ስምምነት ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ስለ ስምምነቱ እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ሀይሎች መካከል የተካሄደው የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም አስገኘ? በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ ለቃል አቀባዩ ተነስቶላቸዋል።

አምባሳደር መለስ በምላሻቸውም ” ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነት እንዲቆም ከማድረግ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ላይ ይደርሱ የነበሩ የዲፕሎማሲ ጫናዎች እንዲቀንሱ፣ እንደ አየርላንድ እና መሰል ሌሎች ሀገራት ጋር የነበራት የዲፕሎማሲ መሻከር እንዲስተካከል አድርጓል” ብለዋል።

እንዲሁም የስምምነቱ መፈረም እንደ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት እና ተቋማት ጋር መልካም ትብብሮችን መፍጠር አስችሏልም ብለዋል አምባሳደር መለስ።

የስምምነቱ ስኬታማነት በአንድ ዓመት ውስጥ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ብቻ የሚወሰን አይደለም የሚሉት አምባሳደር መለስ በቀጣይ ጊዜዎች ቀሪ የስምምነቱ ትግበራዎች እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በሰላም ስምምነቱ ላይ ከተኩስ ማቆም ባለፈ ተዋጊዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው እንዲመለሱ የስነ ልቦና እና የኢኮኖሚ ድጋፍ ማድረግ፣ የተቋረጡ መሰረተ ልማቶችን ዳግም ስራ ማስጀመር እንዲሁም የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን ቦታዎች መመለስ የሚሉ ጉዳዮች ቢካተቱም እስካሁን አልተፈጸሙም።

ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢቆምም በአማራ ክልል አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።

አሁን ላይ የአማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሲሆን በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *