የግብርና ሚንስቴር እንደገለጸው በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሳ እና ስጋት እየሆነ በመምጣቱ በዓመት እስከ 2 ሺህ 7 መቶ የሚደርሱ ሰዎች ይሞታሉ።
በሚኒስቴሩ የእንስሳት ጤናና ፐብሊክ ሄልዝ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ እንደተናገሩት ሁኔታው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች ትልቅ ስጋት ሆኗል፡፡
በከተሞች አካባቢ ባለቤት አልባ ውሾች በየመንገዱና በየጎዳናው የሚስተዋሉ በመሆናቸው በርካታ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ ተጠቂ እየሆኑ ነው ተብሏል።
እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በበሽታው በስፋት እንደሚጠቁም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በሽታውን ለመከላከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱ ውሾች ቢከተቡ በሽታው ከውሻው ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻልም ተገልጿል።
አስቀድሞ በሽታው በሰዎች ህይወትና ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ኢትዮጵያ የአንድ ጤና ዘዴ (One Health) በመጠቀም በ2030 የውሻ በሽታን ለማስወገድና ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶችን ቀይሳ እየሰራች ትገኛለች ተብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የእብድ ውሻን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ከ347 ሺ በላይ ውሾች ተከትበዋል ተብሏል።
የእብድ ውሻ በሽታ በዓለማችን ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም አህጉር እንደሚከሰት የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
እስያ እና አፍሪካ የእብድ ውሻ በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያለባቸው አህጉራት ሲሆኑ ምዕራብ አውሮፓ፣ ሲንጋፖር እና ኒውዝላንድ ደግሞ የእብድ ውሻ በሽታ ስጋት የሌለባቸው ሀገራት ናቸው።