የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ከሁለት ወራት የእረፍት ጊዜ በኋላ ተከፍቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የመንግስትን የአንድ ዓመት የትኩረት መስኮች ይፋ አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው ላይ ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጠረናቀቁ ትልቁ ስኬት ነበር ብለዋል፡፡
90 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው የህዳሴው ግድብ የሲቪል ምህንድስና ስራ ሙሉ ለሙሉ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
ይህ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የሚያመነጭ ግድብ ሳይሆን የቱሪዝምና የውሃ ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሞራል ልዕልና ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለውም መንግስት በተያዘው ዓመት የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ የስራ እድል ፈጠራ ፣ የምግብ ዋስትና እና መልካም አስተዳድር ልዩ ትኩረት የሚሰጥባቸው ዋና ዋና ስራዎች እንደሚሆኑም በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ መታቀዱንም ፕሬዝዳንቷል አክለዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ከሀገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ በተጨማሪ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ የስራ እድል መፈጠሩ ትልቅ ስኬት እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታው 91 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
ኢትዮጵያዊያን በሚያዋጡት ገንዘብ እና በመንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በ5ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው።
የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 350 ሜጋ ዋት ሀይል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል።
ግድቡ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።