በኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተም ወንጀል የተጠረጠሩ ቻይናዊያን በቁጥጥር ስር ዋሉ

በርካታ መጠን ያላቸው የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ቻይናዊያን ባለሀብቶች ንብረት የሆነው ፀሃይ ሪል ስቴት በዚህ ወንጀል እጁ እንዳለበት ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ የሪል ኢስቴቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኪያ ዦንግን ጨምሮ ዘጠኝ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ፖሊስ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች ውስጥ ሶስት ኢትዮጵውያን ተጠርጣሪዎችም ተይዘዋል።

ፖሊስ ሁሉንም ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፖሊስ ግለሰቦቹ በርካታ መጠን ያላቸው የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል መጠርጠራቸውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች የሚታተሙባቸው ማተሚያ ማሽኖችና ለግብዓት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ ዩሮ፣ የአሜሪካ ዶላርና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች መያዙን ፖሊስ ጠቅሷል።

ተጠርጣሪዎቹ ላይ የተጀመሩ ሰፊ የምርመራ ስራዎችን አከናውኖ እና የተናጠል ተሳትፏቸውን ለይቶ ለመቅረብም የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የግለሰቦቹ የወንጀል ተሳትፎ ባልተገለጸበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

የፀሃይ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ኪያ ዦንግን የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው የተገኘው የውጭ ሀገራት ገንዘብ ማተሚያ በመኖሪያ ቤታቸው እና ቢሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *