በትግራይ የሚገኙ የፖሊስ አባላት ከብልፅግና ፓርቲ ደሞዝ ስትቀበሉ ነበር በሚል እና የትጥቅ ትግሉን አልተቀላቀላቹም በማለት ከስራ እና ከደሞዝ እንዲታገዱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች እስከ 30 ዓመት ድረስ በተለያዩ የትግራይ አካባቢ ተመድበው በፖሊስነት ስራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ የቀድሞ የትግራይ ፖሊስ አባላት፥ ከስራ እና ደመወዝ ውጭ እንዲሆኑ የተደረጉት ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ ባለው ጊዜ መሆኑ ነግረውናል።
እንደ ፖሊሶቹ ገለፃ በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ መከላከያ ትግራይን ሲቆጣጠር አቋቁሞት በነበረው ግዚያዊ አስተዳደር ጋር አብራችሁ ሰርታችኋል የመንግስትን ደሞዝም ተቀብላችኋል በሚል መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በ2013 ዓ.ም በርሃ የነበረው የህውሀት ምክር ቤት በዶ/ር ድብረፅዮን ፊርማ በተረጋገጠ ደብዳቤ ነባሩን የፖሊስ አባል በመሰረዝ አዲስ ማቋቋሙን በመግለፅ ከህግ ውጪ ያለ ስራ እንዲቀመጡና ለከፋ ችግር እንደዳረጋቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ነባር የፖሊስ አባላቱ በተደጋጋሚ የፖሊስ ኮሚሽን በመቅረብ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም የተሰጣቸው ምላሽ ኮሚሽኑ እነሱ መበተናቸውንና አዲስ የተቋቋመውን አባላት እንደሚያውቅ እንዳሳወቃቸው ይናገራሉ፡፡
የፖሊስ አባላቱን ቅሬታ በመያዝ በኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የትግራይ ቅርጫፍ ግዚያዊ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ፀሀዬ እምባዬን የጠየቀ ሲሆን እሳቸውም ፖሊሶቹ አንድ ደብዳቤ ከኮሚሽኑ እንደተሰጣቸው ነግረውናል፡፡
ተቋሙ በአሰራሩ መሰረት መሄድ ስላለበት ፖሊሶቹ ከግዚያዊ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው ምላሽ ከተመለከተ በኃላ ወደ ምርመራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
ከ200 በላይ የሚሆኑት እነዚህ ነባር የፖሊስ አባላት በአሁን ሰዓት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውንና የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡