ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የቆየውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ በአዲሱ በጀት ዓመት እንደገና ለማስጀመር በጀት መያዙን ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል ።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በ48 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባውና 62ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታን ለማስቀጠል በ2016 ዓ.ም በጀት የተያዘለት በመሆኑ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ግንባታው ይጀመራል።
የብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ በቻይናው ኩባንያ ይካሄድ እንደነበረ አስታውሰው፤ ግንባታው በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ገልፀዋል።
በኋላም የግንባታ ተቋራጩ ለሥራው ያቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ከገበያ በላይ የተጋነነ በመሆኑ መንግሥት ከያዘው በጀት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም። በዚህም ከግንባታ ተቋራጩ ጋር ያለው ውል እንዲቋረጥ መደረጉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ተቋራጩ ኮቪድ-19ን እንደ ምክንያት በማድረግ ስራውን አቀርጦ በመቆየቱ ግንባታውን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበር የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ለተቋራጩ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው አስታውሰዋል።
የግንባታ ተቋራጩ ለሥራው አሳማኝ ያልሆነና ከገበያ በላይ የሆነ የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ መጠየቁን አንስተው፤ የተጠየቀው የዋጋ ማስተካከያ የተጋነነ በመሆኑ ብዙ ድርድር በማድረግ ውል ከማቋረጥ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳያጋጥሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል።
በዚህም ከተቋራጩ ጋር የነበረው ውል በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም መቋረጡን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ግንባታውን የጎበኙ የውጭ ሀገር ባለሙያዎች አስተያየትም ሥራው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መከናወኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ስታዲየሙ በውስጡ በርካታ ነገሮችን የያዘ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው፤ የበጀት እጥረት ችግር ካላጋጠመ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።
የስታዲየሙን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ለማስቀጠል ምን ያህል በጀት እንደተያዘ ይፋ አልሆነም።
የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር በጀት ታህሳስ 2008 ዓ.ም እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በጀት መጋቢት 2012 ዓ.ም ተጀምሮ በ900 ቀናት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞም ነበር።