ቻይና ዋነኛዋ የኢትዮጵያ አህያ ስጋ የተላከባት ሀገር ስትሆን ፍላጎቱ እያደገ እንደሆነም ተገልጿል።
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የአህያ ስጋን ወደ ሆንግኮንግ በመላክ 3 መቶ ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የእንስሳት ልማት ኢንስትቲዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስትቲዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሳህሉ ሙሉ እንደተናገሩት፣ ከአህያ ስጋ ውጪ የአህያ ቆዳን እንደ ቻይና ያሉ ሃገራት ለመድሃኒትነት በስፋት ሲጠቀሙበት የሚስተዋል በመሆኑ የስጋ ምርቱን ወደ ሆንግኮንግ እንዲላክ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ገቢው የተገኘውም በተጠናቀቀው በጀት አመት 140 ቶን የአህያ ስጋ ምርትን ወደ ውጪ ገበያ በመላክ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በበጀት አመቱ 600 ቶን የአህያ ስጋን ወደ ውጪ ለመላክ አስቀድሞ ታቅዶ እንደነበር ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
በአህያ ስጋ የወጪ ንግድ ዙሪያ የቄራ ድርጅቶች የማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት የነበረባቸው በመሆኑ ምርቱ ከአመቱ አጋማሽ በኃላ ለአለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲኖረው አስገድዷል፡፡
ይኸው ችግር በዘንድሮው አመት በታቀደው ልክ ገቢ እንዳይገኝ ያደረገ ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በዘርፉ ከተስተዋለው የማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት አኳያ በዘንድሮ በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ተገኝቷል የተባለ ሲሆን ባለፈው በተመሳሳይ ወቅት ከአህያ ስጋ የውጪ ንግድ ሽያጭ 2 መቶ ሺህ ገደማ ዶላር ገቢ ተገኝቶ እንደነበር ዶክተር ሳህሉ ሙሉ አስታውሰዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት አመት ከአህያ ስጋ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ እንዳለው ያሳያል፡፡
ከማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታትም ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎች በመሰራታቸው እና ለቄራ ድርጅቶች አስፈላጊው ግብአት እንዲሟላላቸው በመደረጉ ከአህያ ስጋ የወጪ ንግድ የተሻለ ውጤትን ማግኘት ተችሏል፡፡
በሚቀጥሉት ዓመታት ከዘርፏ የተሻለ ገቢን ለማግኘትና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያስችሉ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት ታቅዷል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሳህሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡