ኢትዮጵያ ለቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የ36 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች

በጀቱ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የ36 ሚሊዮን በጀት ስምምነቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ ለማድረግ ይውላል ተብላል።

በኢትዮጵያ 22 በመቶ ሴቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነላቸው ሲሆን በጀቱ ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በበጀት ስምምነቱ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማጠናከር እንቅፋት ከሆኑ ችግሮች መካከል አገልግሎቱ በነፃ የሚሰጥና ወጭው በአብዛኛው  በለጋሽ አካላት የሚሸፈን በመሆኑና ከለጋሽ አካላት የሚገኘው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት በመኖሩ ለግብዓት የሚያስፈልግ የበጀት ዕጥረት ማጋጠሙን የጠቆሙት ሚንስትሯ ችግሩን በመቅረፍ አቅርቦቱን እንዳይቆራረጥ ለማድረግ  በመደበኛነት ከሚመደበው በጀት በተጨማሪ ለቀጣይ ሶስት አመት መንግሥት 11.27 ሚሊዮን ዶላር አጋር አካላት ደግሞ 24.8 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ የ36 ሚሊዮን ዶላር የተጨማሪ በጀት  ስምምነትና ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መደረጉን ገልፀዋል።

አያይዘውም የቤተሰብ ዕቅድ የእናቶችና የሕፃናትን ሕይወት እንደሚታደግ የገለፁ ሲሆን ሴቶች አቅደው መውለድ ሲችሉ በትምህርት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ተሳትፎ የላቀ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ጠቅሰው በፕሮግራሙ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር አካላትን አመስግነዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው በትንሽ ኢንቨስትመንት ብዙ እናቶችን መታደግ እንደሚቻል ጠቁመው በሶማሌ ክልል በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝት በተደረገ ርብርብ በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ የነበሩ በርካታ እናቶችን መታደግ መቻሉን ማየታቸውን ተናግረዋል።

በመንግሥት በኩል ስምምነቱ የፈረሙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ሲሆኑ በአጋር ድርጅቶች በኩል ደግሞ ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን (BMGF) ፣ በፌት ፋውንዴሽን (STBF) ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና የፓካርድ ፋውንዴሽን (DLPF) ሲሆኑ የኔዘርላንድ መንግስትም (EKN) በቀጣይ በጀት ለመስጠት የስምምነቱ አካል ሆኖ ፈርሟል።

የሲቪክ ማህበራትን በመወከል ደግሞ የስነተዋልዶ ጤና ማህበራት ጥምረት (CORHA) ተገኝተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *