በመተከል ዞን በጉምዝ ታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 18 ደረሰ

በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በጉምዝ ታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 18 ደረሰ

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ግድያው የተፈጸመው አርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 ሲሆን፤ ከ8 በላይ ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

እንደነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ የችግሩ መነሻ፤ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለሥራ በወጣበት ተገድሎ በመገኘቱ አስከሬኑን ለማምጣት በሄዱ የጸጥታ አካላት ላይ በአካባቢው የሚገኙ የጉምዝ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈታቸው ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል፡፡

ተኩሱን የከፈቱት ሽፍታ የነበሩ እና የሰላም ተመላሽ ተብለው ትጥቃቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ከተጠየቁ ታጣቂዎች መካከል ትጥቅ ያልፈቱ እና በጫካ የሚኖሩ ታጣቂዎች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

ተኩሱ የተከፈተው አርብ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ በተከፈተው ተኩስ አራት የጸጥታ አካላትና 14 በትራንስፖርት መኪና ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ተገድለዋል ተብላል።

ግድያው የተፈጸመው ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ፓዊ መወጫ ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራ ቦታ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከተገደሉት 18 ሰዎች በተጨማሪ ከ8 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሶ ወደ ፓዊ ሪፈራል ሆስፒታል መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በግልገል በለስ ከተማ እና አካባቢዋ የትራንሰፖርት እና የሰው እንቅስቃሴ መታገዱን አክለዋል፡፡

ሥማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ የፖሊስ አባል፤ አርብ ዕለት በተከፈተው ተኩስ ማታ ላይ ከአንድ አካባቢ ከአራት በላይ ሰዎች ሞተው መገኘታቸውን ጠቁመው፤ የጸጥታ አካላት ወደ አካባቢው ሄደው የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

“በታጣቂዎቹ በተከፈተው ተኩስ ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን በትክክል አልታወቀም።” ሲሉም የፖሊስ አባሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አካባቢው ባለፉት ተከታታይ ሦስተትና አራት ዓመታት በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ ከቆየ በኋላ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምንት ማድረጋቸውን ተከትሎ የሰዎች ግድያ ቆሞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ ትጥቅ አለመፍታታቸውን ተከትሎ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ስጋቶች ቀጥለው ነበር።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ሆነ የመተከል ዞን አስተዳድር በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን መግለጫ አልሰጡም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *