ግለሰቡ በአንድ ዓመት ውስጥ የገናን እና ፋሲካ በዓል ሎተሪን አሸንፈዋል
አቶ መሃመድ አህመድ አህመድ ይባላሉ፤ተወልደው ያደጉት ጎንደር ነው፡፡
አቶ መሃመድ ሙሉ ስማቸው መሃመድ አህመድ ቢሆንም በተደጋጋሚ ሎተሪ ስለጎበኛቸው የአባታቸው ስም ወደ ሎተሪ ተቀይሮ በሚኖሩበት ከተማ መሃመድ ሎተሪ እየተባሉ በመጠራት ላይ ናቸው፡፡
አቶ መሃመድ ሎተሪ 15 ጊዜ የሎተሪ እድል አሸናፊ መሆናቸውን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር መረጃ ያመላከታል፡፡
ከ1977 አመት ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ሎተሪ ቆርጠው ያጡት ብር እንደሌለ እኝህ አባት ይናገራሉ፡፡
አቶ መሃመድ ከ500 ብር ጀምሮ እስከ 75ሺህ ብር ድረስ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
የእኝህ አባት እድለኝነት የሚያስገርመው ደግሞ የገና ሎተሪ እጣ አሸናፊ ሆነው በዛው አመት በፋሲካም አሸናፊ መሆናቸው ነው፡፡
በሎተሪ ተስፋ ቆርጠው የማያውቁት አቶ መሃመድ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ለሶስት ተከታታይ አመታት ሎተሪ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ መሃመድ ለብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሲናገሩ በሕይወት እና በሎተሪ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሎተሪ እጣ ቆርጠው በተከታታይ እድል የጎበኛቸው ዜጎች እጅግ ጥቂት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በመላው አለም ከሚገኙ ሎተሪ አሸናፊዎች መካከል እስካሁን ድረስ በተደጋጋሚ የሎተሪ እድል አሸናፊ ሆነዋል የሚባሉት የሮማኒያው ግለሰብ አንድሪያ ቫሲል ሲሆኑ 14 ጊዜ አሸናፊ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡