በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ 100 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በአንድ ዓመት ውስጥ ደግሞ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰላም ጥናት ማዕከል አስታውቋል

የኢትዮጵያ ፒስ ኢብዘርቫቶሪ የተሰኘው ተቋም ባወጣው ሪፖርት መሰረት በአንድ ሳምንት ውስጥ 100 ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል ብሏል።

ከሰኔ 3 ቀን እስከ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተፈጠሩ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት 100 ሰዎች መገደላቸውን የግጭት ሁኔታ መረጃዎችን የሚያቀርበው “ኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ” አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የግጭት ሁኔታ እና የክስተት የመረጃ በመሰብሰብና በመተንተን የሚታወቀው “The Armed Conflict Location & Event Data Project” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ይህንኑ ሥራ በኢትዮጵያ እንዲሠራ በፕሮጀክት ደረጃ ያቋቋመው፣ “Ethiopia Peace Observatory” የተባለው ተቋም ባወጣው ሳምታዊ ሪፖርት፤ በሳምንቱ ከተገደሉት 100 ሰዎች መካከል 35ቱ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

በሳምንቱ 19 የፖለቲካ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች መከሰታቸውን የገለጸው ሳምንታዊ ሪፖርቱ፤ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎ መካል ውጊያዎች ሲደረጉ እንደነበር ጠቁሟል።

በኹለቱ ክልሎች አለመረጋጋት እንደቀጠለ ሲሆን፤ በሌሎች አካባቢውች ደግሞ በአንጻሩ ሰላማዊ ሁኔታዎች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡ በአማራ ክልል የተከሰቱ የፖለቲካ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች መንግሥት “በጽንፈኛ ኃይሎች” ባላቸው አካላት ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ተቋሙ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መቀጠላቸውን የተቆመው የተቋሙ ሳምንታዊ ሪፖርት፤ ባለፈው ሳምንት በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በ“ኦነግ-ሸኔ” መካከል ሰባት የውጊያ ኩነቶችን መመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡

ከሰኔ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም ባለው አንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ በ1 ሺሕ 103 የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት 5 ሺሕ 676 ሰዎችን ሞት ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ከሟቾቹ መካከል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች 2 ሺሕ 587 መሆናቸውን ይሄው ተቋም በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *