በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለችው ሱሉልታ ከተማ በርካታ ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች ታገቱ

በቅርቡ በተዋቀረው የሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኘው የሱሉልታ ክፍለ ከተማ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸው ተገልጿል።

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ በሱሉልታ ክፍለ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት በሚጠራው እና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በመባል በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን የሚፈጸሙ መሰል ድርጊቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም “ከአንድ ሳምንት በፊት በአንድ ምሽት ብቻ ከሱሉልታ ክፍለ ከተማ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን አካባቢ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል” ሲል አዲስ ማለዳ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

ሰዎቹ በተወሰዱበት ዕለትም ምንም አይነት የመሳሪያ ድምጽ ባለመሰማቱ የጸጥታ አካላት ደርሰው ሊያስጥሏቸው እንዳልዳቻሉ ጠቅሰዋል።

ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን 2015 እንዲሁ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ምሽት ላይ ታግተው መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የተወሰዱት ሰዎችም እስካሁን ድረስ ያሉበት አይታወቅም የተባለ ሲሆን፤ አጋቾችም ይህን ያህል ብር አምጡና እንለቃቸዋለን በማለት እየተደራደሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ነዋሪዎቹ ታጣቂ ቡድኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአካባቢው እና በሌሎች አዋሳኝ ወረዳዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የተናገሩ ሲሆን፤ ትግሉም ከሌላ አካል ጋር ሳይሆን ንጹሃን ዜጎችን እያፈነ ገንዘብ መጠየቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የሱሉልታ ክፍለ ከተማ የሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታገል መለሠ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ምላሽ ሊሰጡ እንዳልቻሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *