በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ባለው አንዋር መስጅድ ዛሬ ምሳ ሰዓት አካባቢ የጸጥታ ችግር መከሰቱ ይታወቃል።
ለአርብ ወይም ጁመዓ ጸሎት በስፍራው የነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንዳሉን ከሆነ የሶላት ስነ ስርዓቱ ተጠናቆ ወደ ውጪ እየወጡ እያለ ከጸጥታ ሀይሎች ጥይት መተኮሱን ተከይሎ በአካባቢው ችግር ተፈጥሯል።
ለደህንነቱ በመፍራት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአይን እማኝ ለአልዐይን እንዳለው ” በአንዋር መስጅድ የጁመዓ ስግደትን ስግደት ጨርሰን ወደ ውጪ እየወጣን እያለ ፖሊሶች ጥይት ተኮሱ፣ ከዚያም ሰዎች መውደቅ እና መጮህ ጀመሩ” ሲል ነግሮናል።
“አጠገቤ የነበሩ ሁለት ሰዎች እጅ እና እግራቸውን በጥይት ተመተው ሲወድቁ አይቻለሁ” ያለን ይህ የአይን እማኝ እኔ ወደ መስጅዱ ተመልሼ በመግባቴ ተርፌያለሁ ሲልም የአይን እማኙ አክሏል።
“ምንም አይነት ተቃውሞ ባልነበረበት ሁኔታ ስግደቱ ካለቀ በኋላ በሰላም ወደ ውጪ እየወጣን እያለ ፖሊስ ጥይት ተኮሰብን” ያለው ደግሞ ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ እማኝ ነው።
እማኙ አክሎም ” አጠገቤ የነበረ ሰው ደረቱን በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል፣ ቆስለው ደም ሲፈሳቸው የነበሩ ሌሎች ሰዎችንም አይቻለሁ” ያለን እማኙ የተጎዱ ሰዎች ለረክም ጊዜ ደም ሲፈሳቸው ነበር ወደ ህክምና የተወሰዱትም ዘግይተው መሆኑንም ጠቅሶልናል።
ሶላት ማለቁን ተከትሎ ከመስጅድ ወጥተቅ የነበሩት ሰዎች ዋነኛ ተጎጂ ሆነዋል ያለን የአይን እማኙ መስጅዱ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አሁንም መውጣት እንዳልቻሉ፣ በረሀብ እና በድካም እየተጎዱ እንደሆነም አክሏል።
አልዐይን አማርኛ ስለ ጉዳዪ የአዲስ አበባ ፖሊስን የጠየቀ ሲሆን በተከሰተው ክስተት ዙሪያ በቅርቡ ለህዝብ ማብራሪያ እሰጣለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት በተመሳሳይ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
ፖሊስ አክሎም በተፈጠረው የጽጥታ ችግር የጸጥታ ሀይሎችን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም የመቁሰል አደጋ ማጋጠሙን በወቅቱ ገልጿል
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ምክር ቤት በበኩሉ በሸገር ከተማ እየተፈጸሙ ያሉ የመስጅድ ፈረሳዎችን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ ተቃውሟል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ድርጊት ተቀባይነት የለውም ያለው ምክር ቤቱ ያልተመጣጠነ እና ህገወጥ እርምጃ በወሰዱ የጸጥታ ሀይሎች ላይ ቅጣት እንዲጣልባቸውም ጠይቆ ነበር።