ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ዋንጫን አነሳ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ዋንጫን አነሳ፡፡

ከሁለት ጨዋታዎች በፊት ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው የምድብ ሀ የከፍተኛ ሊግ ውድድር የመዝጊያ ስነ-ሥርዓት ላይ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

ቡድኑ ቀሪ የመርሐ ግብር ጨዋታውን ከቀኑ 6፡00 ላይ ከሰንዳፋ በኬ ጋር በማድረግ 4 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነጥቡን 60 ማድረስ ችሏል፡፡

በውድድሩ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመርቻንት እና ኤጀንት ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃ/ሚካኤል እና ሌሎች እንግዶች ለሻምፒዮኑ ቡድን እና ለሌሎች ተሸላሚዎች ዋንጫ እና ሜዳሊያ አበርክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ላደገው  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች እና የቡድን አባላት ምስጋና እና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያሰተላለፉ ሲሆን፣  ባንኩ ቡድኑ በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ስኬታማ እንዲሆን አሰፈላጊውን ሁሉ  እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ለ6 የውድድር ዓመታት ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ርቆ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *