ህወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕልውናዬን የሚያከስም በመሆኑ አልቀበለውም አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉዳይ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

ቦርዱ ከዚህ በፊት ህወሓት ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ ምርጫ በማድረጉ፣ ወደ ትጥቅ ትግል እና አመጽ ተግባር ገብቷል በሚል ፓርቲው እንዲከስም ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡

ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ማመልከቻ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ እና ከሽብርተኝነት መሰረዙን ተከትሎ  በምርጫ ቦርድ የተላለፈብኝ ውሳኔ ይነሳልኝ ሲል አመልክቶ ነበር፡፡

ምርጫ ቦርድም ከዚህ በፊት በህወሓት ላይ ያስተላለፍኩት ውሳኔን መቀልበስ የምችልበት ህጋዊ አሰራር የለም ሲል ምላሽ ሰጥቶም ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎም ህወሓት ከቀናት በፊት ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለው ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ” አልቀበለውም ” ያለው ህወሓት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እወያይበታለሁ ብሏል።

ምርጫ ቦርድም ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶርያ ስምምነትና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያስተላለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ እንዲያስተካክል በድጋሚ ጠይቋል።

ህወሓት የሰላም ስምምነቱ ባለቤት ናቸው ያላቸው የድርጅቱ አባላት፣ የትግራይ ህዝብና የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቦርዱ ውሳኔ የሰላም ሂደቱ ኣደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ በመገንዘብ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

የፌደራል መንግስትም ” ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ በተጀመሩት አወንታዊ የሰላም እና የመደጋገፍ ጥረቶች ላይ ሊያሳድረው የሚችል አላስፈላጊ ጫና መሆኑን በመረዳት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል፡፡

እንዲሁም የፌደራል መንግስቱ ህጋዊ ውሳኔዎችን እና ስምምነቶችን በሁሉም የመንግስት ተቋማት እና አካላት እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊቱን ግምት ውስጥ በማስገባት የቦርዱን ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከህወሓት ህጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉትን ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጮች ተጠቅሞ ነገሮች ቅድመ-ጦርነት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ያድርግ ሲልም አክሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *