ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ”ሳምራ” በሚል የሰየመውን የኢትዮጵያ ቡና ለገበያ አቀረበ

ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹ በካናዳ ተወልዶ ያደገው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ “ዘ ዊክኤንድ”፤ የእናቱን እና የቤተሰቡን ትውልድ አገር ለማክበር በሚል በእናቱ ሥም የሰየመውን ”ሳምራ” የተሰኘ የኢትዮጵያ ቡና ለአለም ዓቀፍ ገበያ አቀረበ።

አቤል ቡናውን ከ“ብሉ ቦትል ኮፊ” ጋር በመተባባር ለሽያጭ ማቅረቡን በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ይፋ አድርጓል።

አቤል ተስፋዬ እና የሪከርድ ኩባንያው በጋራ በመሆን “ብሉ ቦትል ኮፊ” በሚል ሥም ባቋቋሙት ድርጅት ሥር የኢትዮጵያን ባሕል እና የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ደረጃ መሸጥ መጀመራቸውን ገልጿል፡፡

አቤል የ“ሳምራ ቡና” ወደገበያ መግባትን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የኢትዮጵያ ባህል የማንነቴ ወሳኙ አካል ነው” ያለ ሲሆን፤ ከ‘ብሉ ቦትል ኮፊ’ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ባሕል፣ ወጎች፣ እሴቶች እና ቡና ላይ የዓለም አይኖች እንዲያርፉ ለማድረግ በመስራቴ ኩራት ይሰማኛል” ብሏል።

“ሳድግ እናቴ በኢትዮጵያዊያን ባህላዊ የቡና ሥነ ሥርዓት “ቡና ጠጡ” እያለች ስታቀርብ ተመልክቻለሁ።” ያለው አቤል፤ ይህም ስለመጣበት ማህበረሰብ ያለው ግንዛቤ እንዲቀርጽና ኹልጊዜም ማንነቱን እንዲያከብር እንደረዳው ተናግሯል።

አቤል ለቢልቦርድ በሰጠው መግለጫ ሳምራ ኦሪጅን የእርሱ እውነተኛ ስሜት ፕሮጀክት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በእናቱ ሥም የሰየመበት ምክንያትም ለእናቱ እና ለኢትዮጵያዊ የዘር ግንዱ ያለውን ክብር ለመግለጽ በማሰብ መሆኑን አስረድቷል።

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ‘ዘ ዊክኤንድ’ እና እናቱ ከቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ለገበያ እንደሚቀርብ የተነገረውን ቡና በመቅመስ መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ለሽያጭ ከቀረበው ቡና የሚገኘው ገቢም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱ ተነግሯል።

በዚህም ‘ብሉ ቦትል’ ከሚያገኘው ሽያጭ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በዩኤስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል እርዳታ እንዲደርሳቸው ለማድረግ እንደሚለግስም ተገልጿል።

አቤል ተስፋዬ ‘ዘ ዊክኤንድ’ በሙዚቃው ዘርፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ኤምቲቪ፣ ቪኤምኤ እና የአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማቶችን ያገኘ ድምጻዊ ሲሆን፤ በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ሥፍራ በሚሰጠው ሱፐር ቦውል የእግር ኳስ ጨዋታ በእረፍት ሰዓት ላይ በመዝፈንም ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *