በጀነራል አብዱልፋታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ (RSF) መካከል ባለፈው ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ጦርነት አራተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት እስካሁን ከ200 በላይ ዜጎች ሲሞቱ ከ1500 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ከሟቾች ውስጥ ኢትዮጵያዊያንም ያሉበት ሲሆን የአንድ ቤተሰብ የሖነ አራት ዜጎችን ጨምሮ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን መሞታቸው ተገለጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም መቀመጫቸውን በሱዳን መዲና ካርቱም ያደረጉ የውጭ ሀገራት ኢምባሲዎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ፣አውሮፓ ህብረት፣ ኢትዮጵያ እና በርካታ የውጭ ሀገራት ኢምባሲዎች በካርቱም ከተማ እየተደረገ ባለው ጦርነት ሰለባ መሆናቸውን የየሀገራቱ ውጭ ጉዳጠይ ሚኒስቴሮች በትዊትር ገጻቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በካርቱም ያለው ኢምባሲያቸው እና አምባሳደራቸው ጥይት እንደተተኮሰበት ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ውጭ ግንኙነት ኮሚሽነሩ ጆሴፍ ቦሬል በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት በካርቱም ያለው የሕብረቱ ኢምባሲ በታጣቂዎች እንደተተኮሰበት እና ሱዳን የቬና ኮንቬንሽንን እንድታከብር አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ኢምባሲዎችም ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰበት በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮ ነጋሪ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ተመድ በበኩሉ አሁን ላይ በሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ድርድር ለመጀመር ፍቃደኝነት የለም ብሏል።
በሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በሀይል በ2019 ከተነሱ በኋላ የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከስቷል።
ስልጣን የተቆጣጠረው የሱዳን ወታደራዊ አስተዳድር በሲቪል የሚመራ መንግሥት እንዲመሰረት ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ሲጠይቅ ቆይቷል።
ይሁንና የሱዳን ወታደሮች ለሁለት ተከፍለው ስልጣን በሀይል ለመቆጣጠር ወደ ጦርነት ገብተዋል።