መቐለ ዩኒቨርሲቲ በሚቀጥለው ሳምንት ሥራ ይጀምራል መባሉን አስተባበለ

መቐለ ዩኒቨርሲቲ በሚቀጥለው ሳምንት ሥራ ይጀምራል በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ

በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት የመማር ማስተማር ሥራው የተቋረጠው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሥራውን እንደሚጀምር በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘገብ ቆይቷል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት አራት ወራት 24 ሺሕ የሚጠጉ የቀድሞ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ እና ከመስከረም ወር 2016 ጀምሮ አዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል የተገለጸ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት በኩል የሚያስፈልግ በጀት ሁሉ እንደተለቀቀለትም ተነግሯል።

ነገር ግን ይህ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ሰራተኞች እና አመራሮች አረጋግጠዋል። መቐለ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ዜና የሚመለት መረጃ በይፋዊ የፌስቡክ እና የትዊተር አካውንቱ ላይ አላወጣም።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሓጎስ ዩኒቨርሲቲው ሥራ ለመጀመር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የራሱን ጊዜና ሂደት ይወስዳል ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጡት መረጃ ተናግረዋል።

“ሥራውን ይጀምራል፤ ነገር ግን በሚቀጥለው ሳምንት አይደለም። በእርግጥ ይህንን ለማድረግ ወራትን ይፈጃል” ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን ለተማሪዎቹ ያቀረበው ጥሪ እንደሌለ በመግለጽ፤ “እኛ (ዩኒቨርሲቲው ወይም የትምህርት ሚኒስቴር) ተማሪዎቻችንን እንደገና ለመቀበል ዝግጁ ስንሆን ይፋዊ መግለጫ እንሰጣለን” ብለዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *