ኢትዮጵያ 500 ሺህ ሴቶችን ወደ ሳውዲ አረቢያ ልትልክ መሆኗን ገለጸች

ኢትዮጵያ 500 ሺሕ ሴቶችን ወደ አረብ አገር ልትልክ ነው

በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት 500 ሺሕ ሴቶችን ወደ አረብ አገራት በተለይም ወደ ሳውዲ አረቢያ ለሥራ ለመላክ በመንግሥት እቅድ መያዙ ተገለጸ፡፡

ይህን ተከትሎም በአማራ ክልል ኹሉም ዞኖች ሰሞኑን ወደ አረብ አገር ሄደው መስራት ለሚፈልጉ ወጣት ሴቶች ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን ኢትዮ ነጋሪ ሰምታለች፡፡

ለአብነትም በምስራቅ ጎጃም ዞን ሦስት የስልጠና ማዕከላት የተዘጋጁ ሲሆን፣ በሞጣ፣ ደብረ ማርቆስ እና ደጀን ከተሞች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች የቤት አያያዝና ሌሎች አስፈላጊ የሥራ ስልጠናዎች እንደሚሰጡኢትዮ ነጋሪ ከዞኑ መረጃ አግኝታለች፡፡

ስልጠናው ለ20 ቀን በመንግሥት በነጻ የሚሰጥ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ ከስልጠናው በኋላ ፈቃደኛ የሆኑ ሴቶች ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚያቀኑበት የዚህ ዓመት የመጀመሪያው በረራ መጋቢት 26/2015 እንሚጀመርም ተሰምቷል፡፡

ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሴቶች በዩንቨርሲቲም ሆነ በኮሌጅ የተመረቁ፣ ቀደም ሲል ሰልጥነው ያልተሰማሩ እና የመሄድ ፍላጎት ያላቸው፣ የስደት ተመላሽ ሆነው ለመሄድ የሚፈልጉና የወንጀል መዝገብ የሌለባቸው እንዲሁም ስልጠና ወስደው የመሄድ ፍላጎት ላላቸው ነው ተብሏል፡፡

ፍላጎት ላላቸው ሴቶች በኮሌጆች ቅድመ ስልጠና በመስጠት 50 በመቶ ያህሉ መጋቢት 26/2015 በሚጀመረው ጉዞ እንዲሄዱ ከተደረገ በኋላም፤ ቀሪዎቹ ከዚያ ቀጥሎ የሚሄዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ሳውዲ አረቢያ ከአፍሪካ የቤት ሠራተኞችን መቅጠር ካቆመች ከሦስት ዓመታት በኋላ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን መቅጠር ልትጀምር መሆኑን መግለጿ ይታወሳል፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድም በሳዉዲ አረቢያ ያሉ የአሰሪ እና ሠራተኛ ኤጀንሲዎች አዲስ አበባ ባለው የሳውዲ ኤምባሲ በኩል ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማሳሰቢያ ሰጥታለች፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ሲመልስ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በሳውዲ አረቢያ ከ750 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከ450 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ መሆናቸው ይነገራል።

በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ለእስር እና ለከፋ ስቃይ እንደተዳረጉ ይገመታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሪያድ እና በሌሎች የሳኡዲ እስር ቤቶች ውስጥ የሚሰቃዩ  ኢትዮጵያውያን እናቶች፣ ህጻናትና አረጋውያንን በማስቀደም፤ በሳምንት እስከ ዘጠኝ በረራዎችን በማድረግ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *