የፖሊዮ ቫይረስ በኢትዮጵያ ዳግሞ ማገርሸቱ ተነገረ

የፖሊዮ ቫይረስ በኢትዮጵያ እንደገና መከሰቱን ተከትሎ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የሚያካትት የተቀናጀ ሀገር አቀፍ የክትባት ዘመቻን ሊካሄድ ስለመሆኑ ተገልጿል።

ቫይረሱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ አካባቢ፣ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በደራሼና ጎፋ ዞኖች መከሰቱን የገለጸው የኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩት ቫይረሱ ከዚህ ቀደምም በጋምቤላ ክልል በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ፣ በኑዌርና በኢታንግ ልዩ ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቋል።

ቫይረሱ በተከሰተባቸውና ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ አምስት የሀገሪቱ ክልሎች የቤት ለቤት የክትባት ዘመቻ ይካሄዳል ያለም ሲሆን
ዘመቻው ከወርሀ ህዳር አጋማሽ ጀምሮ በሁለት የተለያዩ ዙሮች እንደሚካሄድ ገልጿል።

በዘመቻው በ120 የአዲስ አበባ ወረዳዎች 884 ሺ 323፣ በ81 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ፣ በ276 የኦሮሚያ ወረዳዎች 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ በ91 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ በ61 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች 661 ሺ 539 በድምሩ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በተለይም ሕፃናትን ለመከተብ መታቀዱንም ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው።

ከክትባቱ የቤት ለቤት ዘመቻ ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ የሆኑትን የኢቦላና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ለመከታተል የሚያስችል ቅኝት ይደረጋልም ብሏል።

ሆኖም ክትባቱ ምንም እንኳን በዋናነት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የሚሰጥ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦና ሆለታ አካባቢዎች እስከ 10 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት ሊያካትት እንደሚችል ተገልጿል።

ፖሊዮ በቫይረስ የሚከሰትና በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታ ነው። በዋናነትም ሕፃናትን ያጠቃል። በሽታው የነርቭ ሥርዓትን በመጉዳት የተለያዩ የአካል ጉዳቶችን
የሚያስከትልም ሲሆን ለሞት ሊዳርግ እንደሚችልም መረጃዎች ያሳያሉ።

በሽታው በዋናነት በተበከለ ምግብና ውሃ፣ እንዲሁም ከተበከለ ሰገራ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን በክትባት መልክ ከመከላከል ባለፈ አክሞ ለማዳን የሚያስችል የተለየ ሕክምና እንደሌለ ይነገራል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *