የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክክር ሂደቱን «ተዓማኒነት»፣ «አካታችነት»፣ «ገለልተኝነት» እና «ፍትሐዊነት» ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ተደጋጋሚና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል በሚል ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምላሽ ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ አብን ነሀሴ 08 ቀን 2019 ዓ.ም ላወጣው መግለጫ በሰጠው ምላሽ፣ ፓርቲው ሂደቱ «አካታች» እና «አሳታፊ» አይደለም በሚል ያቀረበውን መግለጫ መመርመሩንና ማጣራቱን ገልጾ፣ የፓርቲውን ድምዳሜ እንደማይቀበለው ይፋ አድርጓል።
ፓርቲው ወደ ምክክሩ የገባው ችግሮች በኃይል ሳይሆን በውይይት፣ በጫና ሳይሆን በመደማመጥ፣ በአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን በጋራ መግባባት፣ እንዲሁም ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንደነበር በመግለጫው አስታውሷል።
ሆኖም በሂደቱ ውስጥ ከተራ የአሰራር ግድፈት የተለየ ሁኔታ መመልከቱን የዘረዘረው አብን፣ ሂደቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ተዓማኒነትን፣ አካታችነትንና ፍትሐዊነትን ያልተከተሉ «ተደጋጋሚ» እና «የተደራጁ» ጥፋቶች ተፈጽመዋል ሲል ከሷል።
ፓርቲው ተፈጽመዋል ያላቸው ጥሰቶች የምክክር ሂደቱ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዳያመጣ ስጋት እንደፈጠሩበት ገልጾ፣ ችግሩ ካልተፈታ ለሂደቱ ውጤት እውቅና እንደማይሰጥም አሳስቧል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ ከአብን እና ሌሎች ፓርቲዎች የቀረበበትን የገለልተኝነት፣ የአካታችነት እና የተሳትፎ ጉድለት ውድቅ አድርጓል።
ከአንድ ወር በፊት ማለትም ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው ጉባዔ ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ባዘጋጀው የአሰራር ስርዓትና ዕቅድ መሰረት «በመልካም» ሁኔታ እየሄደ ነው ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ ምክክሩ የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የተከፈተ «ታሪካዊ» ዕድል እንደሆነ አስረድቷል።
በተጨማሪም ሂደቱ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማምጣት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ ሁሉም አካላት ሂደቱን በባለቤትነት እንዲይዙት ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሂደቱን በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነትና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛልም ብሏል።
የምክክሩ ሂደት የማንኛውም «ፓርቲ»፣ «የመንግሥት አካል» ወይም የተለየ ቡድን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚውል መድረክ አይደለም ያለው ኮሚሽኑ፣ ይልቁንም የተለያዩ ፍላጎቶችና አቋሞች በእኩልነት የሚቀርቡበትና በምክክር የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚሠራበት ሀገራዊ መድረክ መሆኑን አስረድቷል።
የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ አይደለም የሚለውን የአብን አቋም በተመለከተ ኮሚሽኑ ተገቢውን ምርመራና ማጣራት ማድረጉን ጠቅሶ፣ ከምርመራው በኋላ የፖለቲካ ፓርቲውን ድምዳሜ እንደማይጋራው አስታውቋል።
በመጨረሻም በምክክሩ ሂደት እየተሳተፉ ያሉ አካላት ለጉባዔው ስኬት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
በምክክር ጉባኤው ላይ ከተነሱ ቅሬታዎች መካከል የፌደራል ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ዋነኛ የልዩነት መነሻ የሆነ ሲሆን ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል እንድትሆን ያልተገባ ጫና እየተካሄደ እንደሆነ የሚገልጹ ቅሬታዎች በስፋት እየተነሱ ይገኛል።