የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠናን ታሳቢ ያደረገ የባቡር መስመር ትስስር ወደ ሁሉም የጎረቤት ሀገራት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ታሳቢ ያደረገ እና ኢትዮጵያን ከሁሉም የጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስር የባቡር መስመር እየተሰራ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የባቡር ትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ በመሆኑ ረዥም ርቀትን፣ መሰረተ ልማትን እንዲሁም ንግድና ቀጠናዊ ትስስርን ታሳቢ አድርጎ እንደሚሰራ የገለፁት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ናቸው።
በመሆኑም የባቡር መስመር ዝርጋታ በሀገር ውስጥ የሚቆም ሳይሆን፤ በሁሉም አቅጣጫ ከሚገኙ ጎረቤት ሀገራትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ለመነገድና ለመስራት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ባሻገር ደግሞ የአፍሪካን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ከማስፋፋት አንፃር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ሲባል ወደ ሁሉም የጎረቤት ሀገሮች መንገዶች እየተሰሩ መሆኑን የሚገልጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኗን አክለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ለአብነትም ከኬንያ ወደቦች እስከ ሞያሌ ድረስ ያለው መስመር በተሳካ ሁኔታ መሰራቱን አንስተዋል።
“ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል እንደሆነች ሁሉ የቀጠናዊ ትስስሩንም ግንባር ቀደም እየሆነች ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ በባቡር ትራንስፖርት ከጅቡቲ ጋር ትስስር መኖሩን የገለጹ ሲሆን፤ መስመሩ ብቻም ሳይሆን ድርጅቱም በሁለቱ ሀገራት በጋራ እንደሚተዳደር አንስተዋል።
ይህም አንድን ተቋም እና መሰረተ ልማት በጋራ ገንብቶ አብሮ በመጠቀም በኩል ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ይህ የባቡር መሰረተ ልማት እየተስፋፋ ሲሄድ ወደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ኬንያ እና ወደ ሌሎችም ጎረቤት ሀገራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር የሚያስተሳስረው የባቡር መስመር ግንባታ መቼ እንደሚገነባ፣ ወጪው ምን ያህል እንደሚሆን እና በማን እንደሚሸፈን ሚንስትሩ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ መጀመሯ ይታወሳል።
ሀገሪቱ ምርቶቿን ወደ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት በመላክ ላይ ነች የተባለ ሲሆን ምርቶቹ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ በኩል እየተላኩ እንደሆነም ተገልጿል።
ዓ.ም በይፋ መጀመሯ ይታወሳል።
ሀገሪቱ ምርቶቿን ወደ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት በመላክ ላይ ነች የተባለ ሲሆን ምርቶቹ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ በኩል እየተላኩ እንደሆነም ተገልጿል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳሉት ከተላኩት የመጀመሪያ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል ስጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና እና ጥራጥሬ እህሎች ይገኙበታል።
ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ደግኖ የኢትዮጵያ ምርቶሽ የተላከባቸው ሀገራት እንደሆኑ ተጠቅሷል።
ምርቶቹ በአብዛኛው የተጓጓዙት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ አማካኝነት ሲሆን፤ አየር መንገዱ ለነፃ ንግድ ቀጠናው ትግበራ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል አቶ ወንድሙ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን ከፈረሙት 54 ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 28 ሀገራት ድንበሮቻቸውን በመክፈት የትግበራ እርምጃ መውሰዳቸውን አቶ ወንድሙ አስረድተዋል።