ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአለም አቀፍ ደረጃ በውሻ እብደት በሽታ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ህንድ ቀዳሚውን ቦታ ስትይዝ ከአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደሆነች የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የዝግጁነት እና የአቅም ግንባታ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደባልቄ አባተ እንዳሉት የውሻ እብደት በሽታ አሁን ላይ በሀገራችን እየተስፋፋ እየመጣ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ነገር ግን በዛ ልክ ትኩረት እየተሰጠው እንዳልሆነ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 4900 ሰዎች በእብድ ውሻ ተነክሰው የመጡ ሲሆን ምልክት ሳያሳዩ ክትባት እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል::
ከነዚህ መካከል 1 በመቶ ያህሉ ህክምናውን እንዳቆሙ ገልፀዋል::
ከዚህ በፊት የእብድ ውሻ ክትባት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች 13 የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ 23 መድረሳቸውን ገልፀው አክለውም ለበሽታው እንደ ችግር የሚታየው ነገር የክትባት መድኃኒቱ ዋጋ ውድ መሆኑ ተጠቅሷል።
ምልክቶቹ ለማሳይት ጥናቶች እንደሚሉት ከሆነ ከሁለት እስከ ሶስት ወር የሚቆይ ሲሆን ነገር ግን እጅላይ ፣እግርላይ እንዲሁም አንገት ላይ መነከሶች በተለይም ለጭንቅላት ቅርብ የሆኑ ቦታዎች ላይ መነከስ ምልክቱ በአፋጣኝ እንዲታይ እንደሚያደርግ እና ከ5 እስከ 20 ቀን ውስጥ ሊታይ እንደሚቻል አስተባባሪው ተናግረዋል።
የእብድ ውሻ በሽታ በየዓመቱ ከ2700 በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገድል የግብርና ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የግብርና ሚንስቴር እንደገለጸው በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሳ እና ስጋት እየሆነ በመምጣቱ በዓመት እስከ 2 ሺህ 7 መቶ የሚደርሱ ሰዎች ይሞታሉ።
በሚኒስቴሩ የእንስሳት ጤናና ፐብሊክ ሄልዝ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ በወቅቱ እንደተናገሩት ሁኔታው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች ትልቅ ስጋት ሆኗል፡፡