የፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ትናንት ምሽት የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን አትሌቶች ድል ቀንያቸዋል።
ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ ለ19 አመት ተይዞ የነበረውን የ3 ሺህ መሰናክል ክብረወሰን በመስበር አሸንፏል።
ከውድድሩ አስቀድሞ ሪከርዱን እንደሚሰብር ሲናገር የነበረው ለሜቻ በአንድ ወር ውስጥ ሁለተኛ ክብረወሰኑ ሁኖ ተመዝግቧል ።
አትሌቱ 7:51:11 በመግባት ሲያሸንፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አብርሃም ስሜ
8:10:73 የግሉን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ 4ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል ።
ከቀናት በፊት የ1500 ሜትር የአለም ክብረ ወሰን የሰበረችው ኬኒያዊቷ ፌዝ ኪፕዮገን ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋዳደረችበት የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ለ8 ዓመት ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች።
የዚሁ ርቀት ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው እና በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ለተሰንበት ግደይ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።
የ5 ኪሎ ሜትር የአለም ሪከርድ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታየ ደግሞ ውድድሩን ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።
በዚሁ ዳይመንድ ሊግ በ800 ሜትር ኢማኑኤል ዋኒወኒ ከኬኒያ ሲያሸንፍ በ 100 ሜትር ወንዶቹ ኬኒያዊዉ ፈርዲናንድ ኦማኒያላ እና ቦትስዋናዊዉ ሌቲስሌ ቲቦጎ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።