ኢትዮጵያ በግብፅ ለተስተጓጎሉ ፕሮጀክቶች ካሳ ልትጠይቅ ነው

ኢትዮጵያ በግብፅ ምክንያት የተስተጓጎሉ ወይም የተከለከሉ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች ያደረሱትን የኢኮኖሚ ጉዳት እና ያመለጡ የልማት ዕድሎችን የሚያጠና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሟን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ እንዳስታወቁት፣ ኮሚቴው እስካሁን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በግብፅ ምክንያት ተፅዕኖ የወደቀባቸውን ከ22 በላይ የልማት ፕሮጀክቶችን ለይቷል።

አዲሱ ኮሚቴ ማስረጃዎችን በማቀናጀት ኢትዮጵያ ልትጠይቅ የምትችለውን የካሳ መጠን መሰረት በመመርመር ላይ ይገኛል። በጥናት እና ግምገማ ሂደቱም ባለሙያዎች፣ የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ አማካሪዎች እና የህግ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።

ሀብታሙ እንደገለጹት ግብፅ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ ተቃውሞና ወታደራዊ ዛቻ በማቅረብ የፈጸመችውን ተግባር ኮሚቴው በማስረጃነት እያሰባሰበ ይገኛል።

ጥናቱ ተግባራዊ እንዳይሆኑ የተከለከሉ ፕሮጀክቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ አካባቢ ጥበቃ ያደረገችውን አስተዋጽኦ እና የታችኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚያገኙትን ጥቅም ግምት ውስጥ ያካተተ እንደሚሆን ተጠቅሷል።

በዚህም በባሮ፣ በዓባይ እና በተከዜ ተፋሰሶች ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለውሃ ሀብት ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያደረገው አስተዋጽኦ እንደሚገመገም ተገልጿል።

በተጨማሪም የህዳሴ ግድብ የወንዙን ፍሰት በማስተካከል የታችኞቹን ሀገራት የሱዳንና ግብፅን ከጎርፍ አደጋ የመጠበቅና በድርቅ ወቅት የውሃ እጥረትን የመቀነስ ሚና እንዳለው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የካሳ ጥያቄውን የማስከበር ሂደትን በተመለከተ ኢትዮጵያ በቅድሚያ በድርድርና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ አካሄድን የምትከተል ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች አማራጮችንም የምትጠቀም እንደሚሆን ተዘግቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *