በአላማጣ እና አካባቢው በተፈጠረው አዲስ ግጭት ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በተለይም በጸለምት/ጠለምት፣ በመጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ የሰዎችን የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት፣ ነጻነት እና ንብረት መብቶች ሥጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ተብሏል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት በመፈጠሩ ሳቢያ ነዋሪዎች ‘በኮማንድ ፖስት’ ሲተዳደሩ ከቆዩት አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆኑን እንዲሁም በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደቦች መጣላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

ይህ ግጭት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ሰፍኖ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለተጨማሪ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያጋልጥ መሆኑንም አስታውቋል፡፡  

በመሆኑም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከማድረስ እንዲታቀቡ እንዲሁም ለግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን በሕግ መሠረት በምክክርና በመግባባት ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ኢሰመኮ አሳስቧል።

ማናቸውም እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ያከበሩ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በዓለም አቀፍና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነት እና የተመጣጣኝነት መርሖችን ያከበሩ መሆናቸውን እንዲረጋገጥም ጠይቋል።

ኢሰመኮ ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ግጭት በውይይት የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማሀሙድ አሊ የሱፍ ከሰሞኑ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲከበር አሳስቧል፡፡

ሊቀመንበሩ አክለውም ህብረቱ በአሁለቱ አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሰሞንኛ ሁኔታዎችን እየተከታተለ መሆኑን ገልጸው ሁሉም አካላት ግጭቱን ከማባባስ ተቆጠቡ ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ከሰሞኑ የተፈጠሩ ግጭቶች እንዳሳሰበው የገለጸው ህብረቱ ሁሉም ወገኖች የእርስ በርስ መተማንን የሚጎዱ ድርጊቶችን ከማድረግ እና ሀሳበችን ከመሰንዘር እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡

አሁን የተፈጠሩ ችግሮች በህብረቱ አደራዳሪነት በተካሄደው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መርህ አማካኝነት ይፈታሉ የሚል ዕምነት እንዳለውም ሊቀመንበሩ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት የቆመው በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ህዳር 2014 ከተፈረመ በኋላ መሆኑ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *