ድንበር አቋርጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በ38 በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

​የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የጥቅምት 2025 ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት የድንበር ፍሰት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ የታየው የሰዎች እንቅስቃሴ ካለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

በወሩ ውስጥ በአጠቃላይ 45,150 የሰዎች ዝውውር የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በቀን በአማካይ 1,456 ሰዎች ድንበር እንደሚያቋርጡ ያሳያል ነው የተባለው።

ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አብዛኛው ማለትም 78.3 በመቶው (35,341 ሰዎች) ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚወጡ ሲሆን፣ ቀሪው 21.7 በመቶው (9,809 ሰዎች) ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ናቸው።

በጥቅምት ወር ድንበር አቋርጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ካለፈው የመስከረም ጋር ሲነጻጸር የ38 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ይህ የፍልሰት መጨመር በተለይ በሱዳን ድንበር በሚገኘው በመተማ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ የታየ ሲሆን፣ ለዚህም በስደተኞቹ መነሻ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ መባባስና ወቅታዊ ሁኔታዎች እንደ ዋና ምክንያት ተጠቃሽ ሆነዋል።

ከሀገር ወደ ውጭ የሚወጡት ዜጎች በዋነኝነት የሚጠቀሙባቸው የጅቡቲ ድንበር የሆኑት ገላፊ እና ደወሌ እንዲሁም የሶማሊያ ድንበር የሆነው ቶጎ ውጫሌ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ መስመሮች 53.2 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ፍልሰት የተመዘገበባቸው ናቸው ተብሏል።

ስደተኞቹ ለፍልሰት የሚያነሳሷቸውን ምክንያቶች በዋነኛነት ( 59.8 በመቶ የሚሆኑት ) ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ምክንያት ያደአጉ ናቸው።

በመዳረሻ ሀገር ሲታይም፣ አብዛኞቹ ማለትም 14,126 (40 በመቶ) የሚሆኑት የሚሰደዱት ወደ ሳውዲ አረቢያ ለማቅናት ዓላማ ሰንቀው ነው።

ሌሎች ደግሞ ወደ ሱዳን (21%)፣ ኬንያ (10.8%)፣ ጅቡቲ (5.5%) እና ሶማሊያ (4.5%) ለማምራት በመጓዝ ላይ መሆናቸውን ሪፖርቱ በዝርዝር አመልክቷል።

በተለይ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚደረገው ጉዞ አብዛኛውን ጊዜ በየመን በኩል የሚያልፍ በመሆኑ ከፍተኛ ሥጋት ያለው መስመር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *