የጋምቤላ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ “ግጭት እና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው ሀይሎች በሰሞኑ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ትርምስ ፈጥረዋል” ብሏል።
የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር ተባብሮ ያመጣውን ሰላም እና ልማት ወደ ኋላ ለመመለስ እየሰሩ ያሉ እነዚህ በእኩይ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሀይሎች በየቦታው ሰዎችን በመግደል፣ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ፣ የፀጥታ አካላትን እና አመራርን ኢላማ በማድረግ ወደ ለየለት የሕዝቦች እልቂት ለማስገባት የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ እንደሆነም ክልሉ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎችን አድኖ በህግ ቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሆነም ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ አካላት አሁን ላይ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሰፊ ስራዎችን እየሰሩ በመሆኑ ሕዝቡ በመሰል ጥፋት ላይ የተሰማሩ አካላትን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ የክልሉ መንግስት ያሳስባል።
ከዚህ በተጨማሪም ለፀጥታ ስራ ተመድበው ከሚሰሩ የሰራዊት አባላት ውጪ የትኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ ይዞ የሚገኝ እና የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የፀጥታ አካላቱ እርምጃ እንደሚወስድም የክልሉ መንግሥት አሳስቧል።
በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሰዎች ህይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የምን ያህል ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ግን በመግለጫው ላይ አልተጠቀሰም።
በጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ላይ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ፤ በከተማይቱ ከማክሰኞ ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ. ም ረፋድ ጀምሮ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባ ከሆነ
ለከተማይቱ አለመረጋጋት መንስኤ የሆነው የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ኡሞድ ኡጁሉ ግድያ የተፈጸመው ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 7፤ 2018 ከቀኑ አራት ሰዓት ገደማ ነው።
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ኡጉላ ኡጁሉ ግድያውን መፈጸሙን ቢያረጋግጡም፤ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል ተብሏል።