​ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ድንበር ሲያቋርጡ ማሰሯን ገለጸች

አንደ ገልፍ ኒውስ ዘገባ የድንበር ጠባቂዎች ባለፉት አንድ ሳምንት ውስጥ 1,924 ሰዎች ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት ሲሞክሩ በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘዋል ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 62 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን፣ 37 በመቶ የመን እና ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገሮች ዜጎች ናቸው። በተጨማሪም 32 ሰዎች ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘዋል።

​በዘመቻው ወቅት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን በትራንስፖርት፣ በመጠለያ ወይም በቅጥር ሥራ በማገዝ የተጠረጠሩ ተጨማሪ 31 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

​በአሁኑ ወቅት 30,236 የውጭ አገር ዜጎች የሕግ ሂደቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።

​የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ማጓጓዝ፣ ማኖር ወይም በምንም መንገድ መርዳት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት፣ እስከ 1 ሚሊዮን ሪያል በሚደርስ ቅጣት እና ጥቅም ላይ የዋሉ ተሽከርካሪዎች ወይም ንብረቶች በመወረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል አስታውቋል።

​ሳዑዲ ዓረቢያ የመኖሪያ፣ የሥራ እና የድንበር ሕጎችን የሚጥሱ ሰዎችን ለመያዝ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምታደርገው ዘመቻ አካል፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ በጠቅላላው 14,916 የውጭ አገር ዜጎችን ከበርካታ አገራት አባርራለች ሲል የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።

​የጸጥታ ኃይሎች እና የተለያዩ የመንግሥት ኤጀንሲዎች ጥቅምት 26 እስከ ህዳር 4 ባደረጉት የተቀናጀ ፍተሻ በጠቅላላው 22,156 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

​በመንግሥት ስታቲስቲክስ መሠረት፣ ከታሰሩት ሰዎች መካከል 14,027 የሚሆኑት የመኖሪያ ሕግን በመተላለፍ፣ 4,781 የድንበር ደኅንነት ሕግን በመጣስ እና 3,348 ደግሞ የሥራ ሕጎችን በመጣስ ተይዘዋል።

​በሀገሪቱ ውስጥ ከታሰሩት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ውስጥ 22,091 የሚሆኑት የጉዞ ሰነዶችን እንዲያገኙ ወደ የአገራቸው ኤምባሲዎች የተላኩ ሲሆን፣ 4,784 የሚሆኑት ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ 14,916 የሚሆኑት ደግሞ ሁሉንም የአሠራር ሂደቶች ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ይህ በዚህ እንዳለም በአንድ ሳምንት ውስጥ ውስጥ አምስት ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ ተገድለዋል ተብሏል።

ከሰሞኑ ሁለት ጓደኛሞችን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች በተሰነዘረባቸው ጥቃት ሕይወታቸዉ ማለፉን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተናግረዋል።

‎ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያውያንን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በታጠቁ ሰዎች ተደጋጋሚ እንደሚፈፀም ተናግረዉ፤ ይህም የበርካታ ኢትዮጵያዊን ሕይወት መቅጠፉን ገልፀዋል።

‎ለደህንነታቸዉ ሲሉ ማንነታቸዉን እንዲገለፅ ያልፈለጉ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደገለፁት ከሁለት ቀናት በፊት በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ 2 ኢትዮጵያዊያን ጓደኛማቾች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የጆሀንስበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነ የሶስት ልጆች አባት ከስራ ወደቤቱ በሚመለስበት ወቅት በታጠቁ ሰዎች በበርካታ ጥይት ተደብድቦ መገደሉን አስረድተዋል።

‎በሌላ መልኩ አንድን ወጣትና ሌላ ታዳጊ በዚሁ በጁሀንስበርግ ከተማ አቅራቢያ በስራ ቦታ ሱቅ ዉስጥ እያሉ በጠራራ ፀሐይ በታጠቁ ሰዎች በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል ሲሉ ገልጸዋል።

‎በሀገሪቱ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈፀም ቢሆንም አዲስ ዓመት እየተቃረበ ሲመጣ ግድያው እየጨመረ ይመጣል ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ የግድያ ወንጀሎቹን እየመረመረ መሆኑ ያስታወቀ ቢሆንም እስካሁን ተጠርጣሪዎቹ ስለመያዛቸው የተገለጸ ነገር የለም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *