የክልል አየር ማረፊያዎች ዓለም አቀፍ በረራዎች ማስተናገድ ሊጀምሩ ነው

ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተጨማሪ በሌሎች የክልል አየር ማረፊያዎች ማስተናገድ ሊጀመር መሆኑን የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ አበራ፣ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እና የግል አየር ትራንስፖርት ኦፕሬተር ተወካዮች በተገኙበት፤ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የባለድሻ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በባለስልጣኑ የአየር ትራንስፖርትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አማካሪ አቶ እንደሻው ይገዙ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በ2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ ክልል ኤርፖርቶች ማስተናገድ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

“የክልል ኤርፖርቶችን ማስተሳሰር የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር እንዲሁም የደንበኛውን እንግልት መቀነስ የሚያስችል ነው” ያሉት አቶ እንደሻው፤ ለአብነትም ከሚዛን ቴፒ – ጅማ – ጋምቤላ – አሶሳ እንዲሁም ከድሬደዋ – ሃረር – ባሌሮቤ የተሳሰረ በረራ እንዲኖር ለማድረግ መታሰቡን ገልጸዋል።

ይህም አንድ ሰው በሀገር ውስጥ በረራ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ የግድ አዲስ አበባ መምጣት እንዳይኖርበት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ በረራዎች ከአዲስ አበባ ኤርፖርት በተጨማሪ በክልል አየር ማረፊያዎች ለማስተናገድ መታቀዱንም አማካሪው ተናግረዋል።

“ለአብነት ዓለም አቀፍ በረራዎቹን ከባህር ዳር፣ መቀሌ እና ድሬደዋ ቢደረጉ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ልማቱን የሚደግፍ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም መንፈሳዊ ጉዞዎችን ከክልል ኤርፖርቶች ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የሃጂ ኡምራ ጉዞ፣ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ገናን በላሊበላ እና ጥምቀትን በጎንደር ጉዞዎችን ለማስተናገድ መታቀዱን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ወደተሰሩ የቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ ለመብረር አውሮፕላኖች ለማሳረፍ ምቹ መሰረተ ልማት አለመኖር፣ ለግል ኦፕሬተሮች የበረራ ፈቃድ የመስጠት ሂደት መዘግየትና የአውሮፕላን ጥገና መስጫ አገልግሎት እጥረት፣ የግል ኦፕሬተሮች ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት አሰራር አለመኖር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በየጊዜው መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኝ በመሆኑ የግል አየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮችም ወደ ዘርፋ በስፋት ተሳታፊ ቢሆኑ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ አበራ በበኩላቸው፤ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመን አሰራሮችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆንን ገልጸው ለግል ኦፕሬተሮች አሁን የተሻለ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *