ኢትዮጵያ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ የመላክ እቅዷን ሰረዘች

መንግስት  ከኦጋዴን ተፋሰስ የተፈጥሮ ጋዝ በጅቡቲ በኩል በቧንቧ መስመር ወደ ውጭ የመላክ እቅዱን የገንዘብ እጥረትና የትግበራ መጓተትን በመጥቀስ በይፋ ሰርዟል።

በኢትዮጵያ ኢነርጂ አውትሉክ 2025 የተረጋገጠው ይህ ስረዛ፣ በሀገራዊ የኢነርጂ ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያሳይ ሲሆን፣ ከውጭ የመላክ ፍላጎት ወደ ሀገር ውስጥ አጠቃቀም እየተሸጋገረ መሆኑን ያመለክታል ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

“የኢትዮጵያ መንግስት በኦጋዴን ክልል የታቀደውን የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት እና የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ ለመላክ ወደ ጅቡቲ የሚዘረጋውን የቧንቧ መስመር ፕሮጀክት ሰርዟል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በጋራ የተዘጋጀው የኢነርጂ አውትሉክ “የፕሮጀክት ፋይናንስን በማግኘት ረገድ ያሉ ችግሮች እና የፕሮጀክት ትግበራ መዘግየት” መንግስት ፕሮጀክቱን ለመሰረዝ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ያስረዳል።

767 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋው እና በመጀመሪያ በዓመት 460 ፔታጁልጋዝ ለማስተላለፍ ታስቦ የነበረው፣ ይህም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የመጨረሻ የኢነርጂ ፍላጎት 25 በመቶ ጋር እኩል የሆነው፣ የታቀደው የቧንቧ መስመር በፈረንጆቹ 2022 መጀመሪያ ላይ መሰረዙ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት ከሚዲያ እና የኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ከቀጣዩ መስከረም ወር ጀምሮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዳጅ ለገበያ እንደምታቀርብ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ባሉ ከቀናት በኋላ ኢትዮጵያ ከኦጋዴን የምታወጣውን ነዳጅ ለዓለም ገበያ ታቀርብበታለች የተባለው የነዳጅ መስመር ግንባታ መቋረጡ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊ ክልል ኦጋዴን አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እንዳላት በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን የቻይናው ፖሊጂሲኤል ኩባንያ ነዳጅ ለማውጣት በሂደት ላይ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሀገራት በማስገባት በመሸፈን ላይ ስትሆን በዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

ላለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ ከውጭ ተገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባው ነዳጅ ላይ የዋጋ ድጎማ ታደርግ የነበረ ሲሆን ከሐምሌ ወር ጀምሮ ግን ይህ ድጎማ ሙሉ ለሙሉ እንደሚነሳና በሀገር ውስጥ የሚቀርበው ነዳጅ በዓለም ነዳጅ ገበያ ዋጋ ላይ እንደሚመሰረት ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *