አደይ አበባ ስታዲየም ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ 18.6 ቢሊየን ብር ተመደበ

ኢትዮጵያ የብሔራዊ ስታድየሟን ግንባታ በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዷ ተገለጸ

62 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው ከተጀመረ 10 ዓመት አልፎታል

በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘውን አደይ አበባ ስቴዲየም ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ 18 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡

አሁን የአደይ አበባ ስቴዲየም ቀሪ ስራዎችን ከሁለት አመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ተብሏል።

የስታዲየሙን የማጠናቀቂያ ሥራዎች ለማከናወን 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ውል መገባቱን የባህልና ስፖርት ሚንስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች አንድ ስታዲየም ያላት ቢህንም ከዚህ ውስጥ አንዱም የካፍን ደረጃ የማያሟላ ሲሆን በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው እና 62 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ አልቻለም፡፡

የብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ በቻይናው ኩባንያ ይካሄድ እንደነበረ አስታውሰው፤ ግንባታው በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል።

የግንባታ ተቋራጩ ለሥራው ያቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ከገበያ በላይ የተጋነነ በመሆኑ መንግሥት ከያዘው በጀት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም በሚል መንግስት ውሉን አቋርጦ ቆይቷል፡፡

የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር በጀት ታህሳስ 2008 ዓ.ም እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በጀት መጋቢት 2012 ዓ.ም ተጀምሮ በ900 ቀናት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞም ነበር።

ይህን ብሔራዊ ስታዲየም ከሁለት ዓመት በታች ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የግንባታ ስምምነት በዛሬው ዕለት መፈረሙ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ በይፋ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም አላት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ጠይቀዋል፡፡

የፊፋ፣ ካፍ እና ሌሎች የእግር ኳስ አመራሮች በአዲስ አበባ በተካሄደው የካፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግስት ለዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች ላይ በተዘጋጀ እራት ግብዣ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ በይፋ ጠይቀዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል  ምስጋና አቅርበው፣ የኢትዮጵያውያን ባህል፣እሴትና እንግዳ ተቀባይነት ኢትዮጵያ  ቤታችን እንደሆነች እንዲሰማን አድርጎናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልዋጸል።

በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሁለቱም ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን መለያን በስጦታ አበርክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ 2029 የሚል ፊርማ ያሳረፉበትን ኳስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አበርክተዋል።

ኢትዮጵያ የካፍን ደረጃ የሚመጥኑ ስታዲየሞች የሌላት በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከሀገሩ ዉጪ በመጫወት ላይ ይገኛል።

የዉድድሩ አዘጋጅ ሀገራት ቢያንስ ስድስት ስታዲየሞችን እንዲያዘጋጁ ካፍ ቢያዝም ኢትዮጵያ እስካሁን የካፍን ደረጃ ያሟላ ስታዲየም የሌላት ሲሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት እያደረገች ስላለው ዝግጅት የተባለ ነገር የለም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *