የአፍሪካ ወጣቶች ሮቦቲክስ ውድድር በአዲስ አበባ ተጀመረ

የአፍሪካ ወጣቶች የሮቦቲክስ ፈጠራ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት 3ኛው የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ዛሬ በታላቅ ድምቀት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል።

የኢትዮ ሮቦቲክስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይክረም መኮንን ለሦስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፈጠራ ችሎታቸው ይወዳደራሉ፤ ውድድሩም በዲዛይን፣ በኢንጂነሪንግ እና በአውቶኖሚ ኮዲንግ ላይ እንደሚያተኩር በመርሃግብሩ ማስጀመሪያ ላይ አስረድተዋል።

አቶ ሰናይክረም የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎት ማዳበርና ማበረታታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆኑ ተማሪዎች የዋንጫ ሽልማት እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተፈረመ የምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።

ለፍጻሜ የሚበቁ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ አቶ ሰናይክረም የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም የተማሪዎች ተሳትፎ ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲቀስሙ እና ከሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎች ጋር እንዲገናኙ እድል ይፈጥሩሏቸዋል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው፣ “የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮንሺፕ ውድድር  ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ፣ ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ ለማብቃት ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለወጣቶች የቴክኖሎጂ ክህሎት እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

ኢትዮ ሮቦቲክስ ለ15 ዓመታት የነገዎቹን ኢንጂነሮችና ፕሮግራመሮች የመፍጠር ራዕይ ሰንቆ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህ ሻምፒዮንሺፕ የዚህ ጥረት አካል ነው ተብሏል።

ባለፈው ዓመት በቻይና ሻንጋይ በተካሄደው ኢንጆይ ኤአይ ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ 21 ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ተሳትፈው ከ27 ሀገራት 3ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የኢትዮ ሮቦቲክስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይክረም መኮንን አውስተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *