አቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን እንዲመሩ ተሾሙ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስተዳድር ወቅት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል፡፡

አቶ ብርሃኑ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በዋና ኮሚሽነርነት ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት እንዲመሩ ተሾመዋል።

ኢሰመኮን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ደናኤል በቀለ (ዶ/ር) በመተካት ሲሆን ተቋሙ ላለፉት ስድስት ወራት በተጠባባቂ ኮሚሽነር ሲመራ ቆይቷል።

ዶ/ር ዳንኤል ባለፈው አመት ሐምሌ ወር የስራ ዘመናቸው ተጠናቆ ከኃላፊነታቸው ከተሰናበቱ ወዲህ የእርሳቸው ምክትል የነበሩት ራኬብ መሰለ፣ ኢሰመኮን የመምራት ኃላፊነት በተጠባባቂነት ተረክበው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ተቋሙ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጀምሮ በሀገሪቱ የተካሄዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን በመመርመር ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እውቅና እንዲደረጉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

አዲሱ የኢሰመኮ ሹመት የፖለቲካ ውግንና ያለባቸው ናቸው የሚል ተቃውሞ በምክር ቤት አባላት የተነሳባቸው ቢሆንም ሹመታቸው በአንላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊትም በተመሳሳይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ሀላፊ መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ባለፉት ዓመታት ከፖለቲካ ውግንና ገለልተኛ የሆኑ አመራሮች ሲመሯቸው የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ ግን አዲሶቹ ተተኪ አመራሮች የፖለቲካ ውግንና አላቸው በሚል ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሚባል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የሀገር ውስጥ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ሪፖርት እያደረጉ ናቸው፡፡

ለአብነትም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ አማራ ክልል እየተፈጸመ ነው ያለውን የጅምላ እስራት ለማስቆም አስቸኳይ አለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል።

ድርጅቱ የሀገሪቱ መንግስት በክልሉ ሰፊ የእስር ዘመቻ ከጀመረበት መስከረም 2024 ጀምሮ አራት ወራት መቆጠራቸውን አመላክቷል፡፡

አምነስቲ ባወጣው መግለጫ  የኢትዮጵያ ፌዴራል እና የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ወደ አራት የጅምላ እስር ቤቶች በማጓጓዝ በክልሉ ውስጥ ማሰራቸውን ገልጿል።

እስር ከተፈጸመባቸው መካከል ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራንን ጨምሮ የፍትህ አካላት ይገኙበታል ተብሏል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ማነስ ተችተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም ወር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር 2017 እንደሚሸፍን በገለጸውና ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ በአማራ ክልል 6 ሺ ሰዎች ለዘፈቀደ እስር ተዳርገዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በሶስት ወራት ውስጥ 120 ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ በዚሁ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

ኢሰመኮ እንደገለጸው ዳንግላ፣ ጭልጋ፣ ኮምቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ዜጎች ከህግ ውጭ በጅምላ ታሰረው የሚገኙባቸው ቦታዎች ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *