መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶች ለመንግሥት ሳያሳውቁ ከከተማ እንዳይወጡ ደብዳቤ ተላከላቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መቀመጫውቸን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ለመንግሥት ሳያሳውቁ ከከተማ እንዳይወጡ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ድንበር ውስጥ ለሚያደርጓቸው ማናቸው እንቅስቃሴዎች ቅድመ ፈቃድ እንዲጠይቁ አሳስቧል፡፡
በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት፣ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች በተመለከተ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተቀመጠ የቅድሚያ ማሳወቂያ ፎርም ከሞሉ በኋላ መሆን እንዳለበት አመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተጻፈው ደብዳቤ ማስጠንቀቂያው ለሥራ ወይም ለግል ጉዳይ የሚጓዙትን እንደሆነ በግልጽ አያስረዳም ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ከዚህ ተመሳሳይ ድብዳቤ ተጽፎ የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንድ ዲፕሎማቶች አሁንም ከፌዴራል መንግሥቱ ዕውቅና ውጭ ሲንቀሳቀሱ በመገኘቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከዓመት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት፣ ክልሎች በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥቱ ብቻ በተሰጠው የውጭ ግንኙነት ሥራ ላይ እየተሳተፉ በመሆኑ ፓርላማው ማሳሰቢያ እንዲሰጥ ተጠይቆ ነበር፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ለሪፖተር በሰጡት አስተያየት፣ ከዚህ ቀደም ዲፕሎማቶች ከከተማ ውጭ ለመውጣት ሲያስቡ እንዲያሳውቁ የተነገራቸው ቢሆንም የተወሰኑ አካላት ያለማንም ዕውቅና ሲንቀሳቀሱ በመታየቱ በድጋሜ ደብዳቤ የተጻፈ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መጣናቀቁን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌና ሌሎች ከተሞች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ዕውቅና ውጭ ሲጓዙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎችም ጭምር ያለ ፌዴራል መንግሥቱ ዕውቅና ተጉዘው ከክልል ባለሥልጣናት ጋር ያደረጓቸው ግንኙነቶች፣ የተወሰኑት ሲዘገቡ የተወሰኑት ደግሞ ከውስጥ በተገኙ መረጃዎች ሚኒሰቴሩ መረጃ እንደሚደርሰው ተናግረዋል፡፡
የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከከተማ ለሥራ ሲወጡ መንግሥት ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ያለበት በመሆኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጳጉሜ 2014 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሁሉም ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በጻፈው ደብዳቤ፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖች በቅጥር ግቢያቸው የሚያደርጓቸውን ስብሰባዎች ከማካሄዳቸው በፊት በቅደሚያ እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡