የቱርኩ ያፒ መርከዚ ኩባንያ በኢትዮጵያ የጀመረውን የባቡር መስመር ግንባታ ሳያጠናቅቅ ከሀገር ወጥቷል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የቱርኩ ተቋራጭ ያፒ መርከዚ ኩባንያ የአዋሽ-ወልድያ-መቀሌ የባቡር ሐዲድ ግንባታን ሳያጠናቅቅ በመውጣቱ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍለው ክስ መመስረቱ ተገልጿል፡፡
ያፒ መርከዚ የተሰኘው የቱርክ ስራ ተቋራጭ ኩባንያ በ2007 ዓ.ም 392 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባቡር መስመር ግንባታ በማካሄድ ላይ ነበር፡፡
ይህ የባቡር መስመር የመካከለኛ እና ሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከጅቡቲ ወደብ ጋር የተሳለጠ የትራንስፖርት እንቅስቀሴ እንዲኖራቸው ታስቦ በመገንባት ላይ ነበር፡፡
ከቱርኩ ኤግዚም ባንክ በተገኘ 1 ነትብ 9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው እየተካሄደ የነበረው ይህ የባቡር መስመር ሊጠናቀቅ ጥቂት መሰረተ ልማቶች ሲቀሩት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
የፒ ኩባንያ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ፕሮጀክቱን አቋርጦ እንዲወጣ እንደተገደደ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 1 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍለው ለንደን በሚገኘው ዓለማቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ክስ መስረቶ በክርክር ላይ ነው፡፡
የግልግል ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን በቀጣዩ ወር ይፋ እንደሚያደርግ የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኮርፖሬሽኑ በብር ምንዛሬ ለውጡ ሳቢያ 264 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበትና ኹኔታው በዚህ ከቀጠለ ሕልውናውን ማስቀጠል እንደማይችልም አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ተቋማቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳትና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት (Damage and Needs Assessment) ማከናወኑን ገልጸዋል ።
በጥናት ግኝቱ መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል።
ለምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተቀመጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ‹‹22 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 20.4 በመቶ የሚገመት ጉዳት›› ደርሷል።
በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።
በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።