ኢትዮጵያ ለአንድ ጊዜ ግልጋሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል ህግ አዘጋጀች፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀም ላይ ገደብ የሚጥል ረቂ ህግ ላይ ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ ባሳለፍነው ሳምንት ለአንድ ጊዜ ግልጋሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል ረቂቅ አዋጅን አዘጋጅቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ እና ተጨማሪ ግብዓት ታክሎበት እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል።
ረቂቅ አዋጁ የሀገሪቱን የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ክምችት፣ መልሶ አጠቃቀም፣ መልሶ ኡደት እና አወጋገድ ሥርዓት ማስያዝ ላይ ያተኮረ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ለሀገሪቱ ፓርላማ የተመራው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ የዜጎችን በንጹሕ እና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ለማረጋገጥ ያለመ ነው ብለዋል።
አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል፤ በዜጎች ጤና እና በሥነ-ምህዳር ላይ ከባድ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ የሚገኘውን የፕላስቲክ ምርት ጉዳት ይቀንሳልም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶችን የመጠቀም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን አንድ ዜጋ በአማካኝ በዓመት እስከ 4 ኪሎ ግራም ፕላስቲክ ምርቶችን ይጠቀማል፡፡
ፕላስቲክ ፓክ ኢትዮጵያ የተሰኘው መንገስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባስጠናው ጥናት ከሆነ በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶች ጥቅም በዓመቱ 11 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡
በ2007 አንድ ኢትዮጵያዊ በአማካኝ በዓመት የሚጠቀማቸው የፕላስቲክ ምርቶች መጠን ከአንድ ኪሎ ግራም በታች ሲሆን ይህ መጠን በ2022 ወደ 3 ኪሎ ግራም ከፍ ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ፕላስቲኮችን ለማምረት ግብዓቶችን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሀገራት የምታስገባ ሲሆን በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና አውሮፓ የምታስገባ ሲሆን በዓመት 224 ኪሎ ቶን ፕላስቲክ ከውጭ ሀገራት በማስገባት ላይ ትገኛለች፡፡
አዲስ አበባ ከፍተኛ የፕላስቲክ ምርት ጥቅም ላይ ከሚውልባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ሲሆን እያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ በአመት እስከ 7 ኪሎ ግራም የፕላስቲክ ምርቶችን ይጠቀማል፡፡