የታክሲ ኮንትራት በመጥራት ሹፌሮችን በመግደል ተሽከርካሪ ሲሰርቁ የነበሩ አራት ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላለፈባቸው
በተለያዩ ጊዜያት አሽከርካሪዎችን ራቅ ወዳለ ስፍራ እየወሰዱ በመግደል ተሽከርካሪዎችን ሲሰርቁ የነበሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
በአዲስ አበባ ገላን ክፍለ ከተማ፣ በሳሪስ እንዲሁም በቢሾፍቱ መኖሪያቸውን ያደረጉት ቴዎድሮስ ብርሃኔ እና እዩኤል ቴዎድሮስ እንዲሁም በሌላ በኩል ተፈሪ ተስፋዬ እና ዩሃንስ አረፋ የተባሉት ግለሰቦች ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ በመመላለስ ድርጊቱን ሲፈጽሙ እንደነበር የሸገር ከተማ አስተዳደር ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ ዓቃቢ ህግ አቶ ሚዴቅሳ አጋሩ ተናግረዋል።
አራት ግለሰቦች ከግል ተበዳዮች በኮንትራት በመውሰድ ከዋናው መንገድ ውጪ በማስውጣት የአሽከርካሪዎቹን ህይወት በማጣፋት ተሽከርካሪዎቹን ይዞ በመሰወር ለተለያዩ ጋራዦች እና ግለሰቦች በመሸጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ እንደነበር ተገልጿል።
ቴዎድሮስ እና እዮኤል የተባሉት ተከሳሾች ሰለሞን አሊ የተባለ የጭነት ተሽከርካሪ አይሱዚ አሽከርካሪን ከዱከም ከተማ እንጨት ትጭንልናለህ በማለት በኮንትራት ዋጋ ተስማምተው ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ያቀናሉ።
በመቀጠል ወደ ሰንዳፋ መስመር እንዲሄድ በጦር መሳሪያ በማስገደድ ጨፌዶሳ የተባለ ቦታ ሲደርስ በሽጉጥ በመምታት ጥለውት ተሽከርካሪውን ይዘው ተሰውረው ቆይተው እንደሸጡት ተገልጿል።
በሌላ በኩል ተፈሪ ተስፋዬ እና ዩሃንስ አረፋ የተባሉት የሁለተኛው የወንጀል ቡድን አባላት ደግሞ አቶ ከበደ በለው የተባሉ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ የሆኑ እና ሃይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ከአዲስ አበባ አሰላ በማሽከርከር የሚተዳደሩ ሲሆን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሰው እናመጣለን በማለት ከወሰዷቸው በኋላ በመሳሪያ በማስገደድ ወደ ገላን ከተማ በመውሰድ በገመድ አንቀው በመግደል ተሽከርካሪውን በጎሮ በኩል ገላን ከተማ በመውሰድ አንዶዴ የተባለው ቦታ አስከሬኑን ጥለው መሰወራቸውን ዓቃቢ ህጉ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪው ሚኪያስ ተስፋዬ የተባለ የ28 ዓመት ወጣት እዮኤል ቴዎድሮስ የተባለው ማታ ላይ ደውሎለት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የምንቀበለው እንግዳ አለ በማለት ምሽት ላይ ቢሾፍቱ ከተማ በተከራዩበት ቤት በመውሰድ በሽጉጥ መግደላቸውን የፖሊስ ማስረጃ አረጋግጧል።
ፖሊስ ባደረገው ክትትል ቴዎድሮስ ብርሃኔ እና እዮኤል ቴዎድሮስ በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ ሂደቱ ሲያጣራ የቆየ ሲሆን በዚህም ሰለሞን የተባለው አሽከርሪውን ገለው ጫካ ውስጥ መጣላቸውን የጭነት ተሽከርካሪውን በ700 ሺህ ብር መሸጣቸውን ለፖሊስ መርተው አሳይተዋል።
በመቀጠል ሚኪያስ ተስፋየ የተባለውን አሽከርካሪ ገድለው እንደጣሉት እና ኮሮላ ተሽከርካሪውን የደበቁበትን ቦታ ለፖሊስ ጠቁመዋል።
ፖሊስ ምርመራውን በመቀጠል የአቶ ከበደ ገዳዮችን ለመያዝ ባደረገው ክትትል አዲስ አበባ ሳሪስ ዶሮ ተራ ከሚባል ስፍራ በመያዝ በሁለቱም ግለሰቦች ላይ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ሃይሩፍ ተሽከርካሪውን እንዲፈታታ በማድረግ ለመሸጥ ሲሞከር በቁጥጥር ስር ለማዋለወ ተችሏል ። በመሆኑም ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በማጠናቀቅ ለዓቃቢ ህግ ይልካል።
ዓቃቢ ህግ ከፖሊስ የደረሰውን የምርመራ መዝገብ በመመልከት ተከሳሾች በመደራጀት የጦር መሳሪያ በመታጠቅ በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው መግደል ወንጀል መፈጸማቸውን በመጥቀስ በወንጀል ህግ 530 መሰረት ክስ መስርቷል።
በዓቃቢ ህግ የተመሰረተውን ክስ የተመለከተው የሸገር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራቱም ተከሳሾች የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት በመመልከት ከባድ እና አደገኛ በመሆኑ የቅጣት ማክበጃ በመጥቀስ በአራቱም ተከሳሾች ላይ በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
በተጨማሪም ተሽከርካሪዎች የደበቁ አራት ግለሰቦች በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን የሸገር ከተማ አስተዳደር ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ ዓቃቢ ህግ አቶ ሚዴቅሳ አጋሩ ተናግረዋል።