በኢትዮጵያ ካሉ የዱር እንስሳት መጠለያዎች ውስጥ አንዱ በሆነው በ ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ከ900 በላይ ዋልያዎች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ 300 ዝቅ ብሏል፡፡
በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መኖሪያቸውን ያደረጉና ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው ከ900 በላይ የነበሩ ዋልያዎች ወደ 306 ዝቅ ማለታቸውን የፓርኩ ፅህፈት ቤት አስታውቋል::
የፓርኩ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ እንደተናገሩት በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግር በተሰማው የተኩስ ድምፅ በፓርኩ ውስጥ የነበሩ ብርቅዬ እንስሳቶች በመረበሻቸው በአሁኑ ሰአት ቁጥራቸው ቀንሷል ብለዋል::
አለመረጋጋቱን ተከትሎ በዋና ዋና የዱር እንስሳቶች መናሃሪያ ቦታዎች ላይ የጦር መሳሪያዎች የነበሩ በመሆናቸው በርካታ የዱር እንስሳቶች ከአካባቢዉ መራቃቸውን የገለፁት ኃላፊው ከእነዚህም መካከል ዋልያዎች ተጠቃሽ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በሚመለከተው አካል በኩል በተደረገው ቆጠራ መሰረት ከእንስሳቶች መካከል የዋልያዎቸ ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ አቶ ማሩ ተናግረዋል።
በአንድ ወቅት በፓርኩ ውስጥ መኖሪያቸውን አድርገው የነበሩ እና ቁጥራቸው ከ900 በላይ የሚልቁት ዋልያዎች በአሁኑ ሰአት ቁጥራቸው ወደ 306 ዝቅ ማለቱ ተገልጿል::
ከዚህም በተጨማሪ ለተኩስ ኢላማ መለማመጃ በሚል እንስሳቶች ላይ የአደን ተግባር ሲከናወን እንደነበር ያወሱት ሀላፊው በተደጋጋሚ ጊዜያቶች የዋልያ እንስሳቶች ለአደን ጭምር የተጋለጡበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል::
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት ላይ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፖርክ ውስጥ ያሉ የዋልያዎች ቁጥር በእጅጉን ቀንሷል።
ሁኔታው ከዚህ በላይ የከፋ እንዳይሆን ለማድረግ የዋልያ ሪከቨሪ ፕላን እቅድ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ከፅህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ይህን ማከናወን የሚያስችል ጥናት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን እንደተጠናቀቀ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል::
እየተዘጋጀ ያለው እቅድ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ በተቋቋመ ቡድን መሰረት ለጊዜው በአካባቢው ላይ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል::
ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአዋጅ ከተቋቋሙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ፓርኮች ዉስጥ ቁጥር አንድ ተጠቃሽ ሲሆን ከጎንደር ከተማ በስተ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ድንቅ እና ማራኪ የመስህብ ስፍራ በ412 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ያለዉ ሲሆን በዓለማችን ካሉት እጅግ አስደናቂና ማራኪ ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎች በኢትዮጵያ ብቸኛ ነዉ፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን አስደናቂ ካደረጉት ነገሮች መካከል አስገራሚ መልክአ ምድራዊ አቀማመጡ፣ የብዝሀ ህይወት ስብጥሩ እነደዚሁም ተራሮች እና ሸለቆዎችን በአንድነት አስተሳስሮ የያዘ መሆኑ ነዉ፡፡ ይህ የቱሪዝም መዳረሻ አቅፎ በያዛቸዉ ብዝኃ ሕይወት ከመላው ዓለም የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ይገኛል፡፡
ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መኖሪያም ሲሆን እንደነ ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉት ብርቅዬ እንስሳት በዚሁ ብሄራዊ ፓርክ ጎጇቸዉን ቀልሰዉ ይገኛሉ፡፡
ከ1ሺህ 200 በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች በፓርኩ ዉስጥ የሚገኙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ፓርኩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ መሆን እንዳለበት በማመን እ.ኤ.አ. በ1978ዓ.ም በቅርስነት መዝግቦታል፡፡
የሰሜን ብሔራዊ ፓርክን መጠለያ ካደረጉት እና ከ200 የሚበልጡት አዕዋፍ ዝርያዎች መካከል አምስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸዉ፡፡