በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ጋምቤላ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ከህግ ውጪ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በንጹሀን ላይ ተፈጽመዋል ብሏል፡፡

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

ጎንደር፣ የጎጃም አካባቢዎች፣ ደብረሲና፣ አታዬ፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎችም ቦታዎች ያሉ ሲሆን መረጃ ለፋኖ ትሰጣላችሁ፣ የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ ናችሁ እና ያለ ምንም ምክንያት ንጹሃን በመኖሪያ ቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያናት እና በጉዞ ለይ እያሉ እንደተገደሉም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይገኙበታል።

ኢሰመኮ አስገድዶ መሰወረንና ሰዎች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየትን በሚመለከት ራሱን የቻለ ዝርዝር መግለጫ በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል። 

ከአማራ ክልል በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ንጹሃን ለሞት እና አካል መጉደል ጉዳት መጋለጣቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ ወለጋ ዞኖች፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና አርሲ ዞን በኦነግ ሸኔ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት ከ45 በላይ ንጹሃን እንደተገደሉ ተገልጿል፡፡

በጋምቤላ ክልል ደግሞ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከ60 በላይ ንጹሃን በመጠለያ ጣቢያዎች፣ መኖሪያ ቤት፣ በትራንስፖርት እና በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል ተብሏል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለገም ተቋሙ ጠይቋል፡፡

እንዲሁም በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡም ተጠይቃወል፡፡

የግጭቱ ተሳታፊዎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ሲልም ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡

በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የመዘዋወር ነጻነትና መጓጓዣ ላይ የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆኑ ገደቦችን ጨምሮ ኅብረተሰቡን ከሚያማርሩ እና ነጻነትን ከሚገድቡ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም ተቋሙ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

ኢሰመኮ አክሎም በተለያዩ ቦታዎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ እና አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሥጋት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርቧል። 

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *