የኤርትራ ሰራዊት ቀደም ሲል ከያዛቸው አካባቢዎች ውጭ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው መባሉን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተባብሏል፡፡
የኤርትራ ሰራዊት ከጦርነቱ ወዲህ የያዛቸውን አካባቢዎች በማስፋፋት ከአዲግራት ከተማ በቅርብ ርቀት በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል መባሉን ያስተባበሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እኔ እስከማውቀው ድረስ የኤርትራ ሰራዊት ከነበረበት አልወጣም አዲስ የያዘውም መሬት ይለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰራዊቱ ቀደም ሲልም ከነበረበት የዛላምበሳ አካባቢ እንዳልወጣ የገለጹት አቶ ጌታቸው እስካሁን ባለኝ መረጃ ወደ አዲግራትም ሆነ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያደረገው አዲስ እንቅስቃሴ የለም ሲሉ ጥያቄውን አጣጥለዋል፡፡
በኤርትራ ሰራዊት የተያዘው አካባቢ የኢትዮጵያ መሬት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን የመከታተል ኃላፊነት መሆን የነበረበት የፌዴራሉ መንግስት እንደሆነ በማስታወስም፤ ሆኖም መንግስት በአካባቢው የነበረውን ሰራዊቱን አስወጥቷል ብለዋል፡፡
የሚከላከለውና የሚጠብቀው አካል ከሌለ ሰራዊቱ የመስፋፋት ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችል ግን አምናለሁም ብለዋል አቶ ጌታቸው፤ የፌዴራሉ መንግስት ሰራዊቱን ከአካባቢው እንዴት እንዳስወጣ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመጠቆም፡፡
የኤርትራ ሰራዊት ይዞታውን ከማስፋፋት በተጨማሪ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ይፈጽማቸዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አዲስ እንዳልሆኑ የተናገሩም ሲሆን ጥሰቶቹ የቆዩና የቀጠሉ ናቸው ብለዋል፡፡
‹‹የኤርትራ ሰራዊት ሲጀመርም ቦታውን አለቀቀም፤ እነዛ ድርጊቶች ድሮ የነበሩ አሁንም የቀጠሉ ናቸው›› ሲሉም ነው አቶ ጌታቸው ስለ ሁኔታው ያስቀመጡት፡፡
ከዛላምበሳ ውጭ አብዛኛው የኢሮብ አካባቢ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ሃይሎች አሁንም በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ይገኙባቸዋል ከሚባሉ የትግራይ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ሰሜን ምስራቅ ዞን በሰዎች ላይ የሚፈጸመው እገታና ግድያ ተባብሶ ቀጥሏል ሲል የዞኑ አስተዳደር ማስታወቁን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡