የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሀይል የማመንጨት አቅም በዕጥፍ ጨምሯል ተብሏል
ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከእጥፍ በላይ ማሳደጓን አስታወቀች።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች አገልግሎት በመጀመራቸዉ ከግድቡ የሚመረተዉ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ወደ 1 ሺሕ 550 ሜጋዋት ከፍ ብሏል።
ከዚሕ ቀደም ሥራ የጀመሩት ሁለት ተርባይኖች እያንዳዳቸዉ 375 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጩ ቆይተዋል፡፡
ሰሞኑን የተመረቁት ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ደግሞ እያንዳዳቸዉ 400 ሜጋዋት ኃይል እንደሚያመነጩ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚያወዛግባትን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት የጀመረችዉ ከመጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ነበር።
ይህ የአፍሪካ ትልቁ ግድብ በ2014 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያዉን ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ግድቡ ከአንድ ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን ከ5 ሺሕ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሏል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ አራት የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡
ኮይሻ ኃይል ማመንጫ፣ አይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ አሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ እንዲሁም አሉቶ ጂኦተርማል የሀይል ልማት ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክቶች በግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሀገራት ከተላከ የኤሌክትሪክ ሀይል 181 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ 140 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል የምትሸጥላቸው ሀገራት ሲሆኑ ወደ ውጭ የተላከው የኃይል መጠን ከ2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የስድስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከመጪው መስከረም ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለታንዛኒያ የ400 ሜጋ ዋት ኃይል ሽያጭ ለመጀመር በተቋም ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱን የኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከስድስት ወራት በፊት በታንዛንያ ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን መንግስት ጋር የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ተቋሙ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ሀገራት እና ለሀገር ውስጥ ደንበኞች ከተሸጠ ኤሌክትሪክ ሀይል 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ሲገልጽ በዓመቱ 817 ሚሊዮን ብር በፀጥታ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ስርቆት ምክንያት መክሰሩን ገልጿል፡፡